የተሃድሶ አይነቶችና ጥያቄዎቻቸው

November 22, 2011

The Fact of the Movement in the Church

አዋልድ መጻህፍት

November 19, 2011

Awalid_Metsahift

ምስጋና

October 31, 2011

ምስጋና
ምስጋና በክርስትና ህይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ነው:: በቤተ ክርስቲያን ጸሎቶቻችን በአብዛኛው በምስጋና ጀምረው በምስጋና ይጨርሳሉ::
ጸሎት ከምስጋና ጋር ነው የሚቀርበው:
ፊል 4:6 ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ።
ባስሊዎስ ቅዳሴ :ለእኛ በጎ ነገርን ያደረገ እግዚአብሄርን እናመሰግነዋለን:: ይቅርባይ የጌታችን የአማላካችንና የመድሃኒታችን አባት ሰውሮናልና ረድቶናልና ጠብቆ አቅርቦናልና:: ወደ እርሱም ተቀብሎናልና አጽንቶ ጠብቆናልና:: እስከዚህ ሰዓት አድርሶናልና:: ስለ ስራው ሁሉ በስራው ሁሉ

በቤተ ክርስቲያን ጸሎቶች በአጠቃላይ በለቅሶ ቤት/ፍትሃት ሳይቀር በምስጋና ይጀመራሉ በምስጋናም ያልቃሉ::
መዝ 7፡17 እግዚአብሔርን እንደ ጽድቁ መጠን አመሰግናለሁ፥ ለልዑል እግዚአብሔርም ስም እዘምራለሁ።

ምስጋና ለአምላክ የሚቀርብ መስዋእት ነው::
መዝ 116: 17 (ሙሉው) ለአንተ የምስጋና መሥዋዕትን እሠዋለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ስም እጠራለሁ። መዝ 107: 22 የምስጋና መሥዋዕትንም ይሠውለት፥ በእልልታም ሥራውን ይንገሩ።
እግዚአብሔርን ልናመሰግነው ከሚገባን ምክነያቶች መካክል: ስለፈጠረን ፡ ስለ ድንቅ ችሎታው ፡ በተፈጥሮችን ስለሰጠን ችሎታዎች፡ በህይወት ስለመኖራችን ፡ ክርስቲያን ስለመሆናችን ፡ እንደ ሃጢያታችን ስላልተመለከተን፡ ጤና ስለሰጠን፡ በህመም ስላስተማረን)

የምስጋና ደረጃዎች : በአመስጋኞችን አይነት በሶስት ከፍለን እናየዋለን (በጥቂቱ ነገር የሚያመሰግኑ፡ ከመከራ ሲወጡ/ ደግ ነገር ሲደረግላቸው የሚያመሰግኑና በመከራ ውስጥም ቢሆን የሚያመሰግኑ)

በመጀመሪያ በማናቸውም ሁኔታ ቢሆን የማያመሰግኑ ሰዎች አሉ:: እግዚአብሄር ታምራት ቢያደርግላቸው ከፈተና ቢያወጣቸውም ምስጋና ትዝ የማይላቸው ሰዎች አሉ::
ዘጠኙ ለምጻሞች የዚህ ምሳሌ ናቸው::
ሉቃ 17፡15_18 ጌታ ካነጻቸው 10 ለምጻሞች ውስጥ ለምስጋና የተመለሰው አንዱ ብቻ ነው:: ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እግዚአብሔርን እያከበረ ተመለሰ፥እያመሰገነውም በእግሩ ፊት በግንባሩ ወደቀ፤ እርሱም ሳምራዊ ነበረ።ኢየሱስም መልሶ፦ አሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ?

ምስጋና የማናመሰግን ሰዎች ችግራችን
• በእኛ አይን ብቻ ስለምናየው ነው (በእነ ማርታ አይን አላዛር ሞቷል በክርስቶስ በኩል ግን ለክብር ነበር)
• የተደረገልንን ነገር ስለማናስተውልም ጭምር ነው (ስለጤናችን ስራ ስለመያዛችን ትዳር ስለመመስረታችን በክርስትና ህይወት ስለመኖራችን ምን ያክል እናመሰግናለን?) እንደ እኛ የሆኑ ብዙዎች ነበሩ ግን እኛ ያለንበት መድረስ ያቃታቸው::

በጥቂቱ የእግዚአብሔር ስራ ምስጋና ከአፋቸው የማይቋረጥ : ከጉንፋን ስለዳኑ ተኝተው ስለተነሱ እግዚአብሔርን የሚባርኩ አሉ:: እኛ ከማናውቀው እርሱ ከሚያውቀው መከራና ፈተና ስለሰወረን::
ስለመፈጠራቸው የሚያመሰግኑ መዝ 139:14 ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። ባለው የሚያመሰግን የሚደሰት ልብ ያስፈልገናል::

ከችግር ከመከራ ከበሽታ ሲድኑ /ስጦታ ሲቀበሉ ምስጋና የሚያቀርቡ:
ከችግር እግዚአብሄር ሲያወጣቸው ከፈተና ሲሰውራቸው ወይንም ልዩ ነገር እግዚአብሔር ሲያደርግላቸው የሚያመሰግኑ አሉ:: አንዱ ለምጻም እንዳደረገው:: ብዙ ክርስቲያኖች ይህንን ያደርጋሉ::
በመከራ ውስጥ እያሉ የሚያመሰግኑ: በዚህ የምስጋና ህይወት የሚታዩ በተለይ ወደ እግዚአብሔር የበለጠ የቀረቡ ቅዱሳን ሰዎች ናቸው:: የስድብና የማንጎራጎር ሳይሆን የምስጋና ቃል ብቻ ከአፋቸው የሚወጣ::
ያእ 5፡11 እነሆ፥ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፥ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና።

በመከራ ሆነው እያመሰገኑ የኖሩትን እናመሰግናቸዋለን በጹአን እንላቸዋለን::

መዝ 33:1 ጻድቃን ሆይ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ ለቅኖች ምስጋና ይገባል።

ምስጋና ለአንድ ቀን ወይም በአንድ ሁኔታ ብቻ የሚቀርብ ሳይሆን በሁሉ ስለሁሉ የሚደረግ ነው
ምስጋና ስለሁሉ በሁሉ
1ኛ ተሰ 5:17 ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና።
ቆላ 3:17 እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ፥ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት።
ስለሁሉ የምናመሰግነው ነገር ሁሉ ለበጎ እንደሆነ ስለምናምን ነው: ሮሜ 8:28 ሆኖም አንዳንዴ ነገሮች ለበጎ መሆናቸውን ለማመን እንቸገራለን
የዮሴፍ መሽጥ ለበጎ ነበረ ነገር ግን ያእቆብም ይሁን ዮሴፍ አልቅሰዋል ዘፍ 37:28
ከእግዚአብሄር የሚሰጠን ሁሉ ለበጎ ነው በክፉዎች ሰዎች ብንወድቅ እንኳን እግዚአብሔር ወደ በጎ ነገር ሊለውጠው ይችላል::
የጎደለን ብቻ ሳይሆን የሆነልንንም እንመልከት:: ወደ ዓለም ምንም አላመጣንም ምንም አንወስድም እግዚአብሔር ግን ብዙ ነገር ስጥቶናል::

እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት መንገድ:
በጸሎት: በመዝሙራችን ፡በንግግራችን፡በሰላምታችን ፡ በአጠቃላይ በልባችን እናመስግን::
ለአለን ነገር ጥሩ ግንዛቤ ይኑረን
የጎደለንን እያሰብን ለማሟላት እንስራ ባለን ነገር ደግሞ እግዚአብሔርን እናመስግን

ገብርሔር

April 5, 2011

(I got this script from someone, I don’t know the writer as well as the person who sent me). I found it biblical and orthodoxy so I post it.

በዲ/ን አባተ አስፋ

ዛሬ ታላቁን የጌታችንን ጾም ከጀመርን ስድስተኛ ሳምንት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህን ሳምንት ቅድስት ቤተክርስቲያን «ገብርሔር» የሚል ስያሜ ሰጥታዋለች፡፡ ገብርሔር በጎ አገልጋይ ማለት ሲሆን የስያሜውን መነሻ የምናገኘው በዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሚነበበው የወንጌል ክፍል ማቴ.25-14-30 ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ መስሎ ካስተማራቸው ትምህርቶች መሀከል አንዱ የሆነው ይህ የዛሬው ወንጌል አስተማሪ የሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮችን በውስጡ ይዟል፡፡ በተለይ ምንም እንኳን የቤተክርስቲያን ሓላፊነት የእገሌና የእገሊት ተበሎ ባይወሰንም ቅሉ ቤተክርስቲያን ባላት የአገልግሎት መዋቅር መሠረት የሓላፊነትን ቦታ ይዘው ለሚያገለግሉ ሰዎች አትኩሮት ሊሰጡባቸው የሚገባቸውን ነጥቦች ይጠቁማል፡፡ ይህን ለማየት ያመቸን ዘንድ ከታሪኩ የመጀመያ ክፍል በመነሣት ዋና ዋና የሆኑ አሳቦችን በአትኩሮት መመርመር ጠቃሚ ነው፡፡ በምሳሌያዊው ታሪክ መጀመሪያ ላይ የምናገኘው አንድ መንገድ ሊጀምር ያሰበ ሰው ከመሔዱ በፊት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን ለአንዱ አምስት ለአንዱ ሁለት እንዲሁም ለሌላኛው አንድ መክሊት ነግደው ያተርፉበት ዘንድ እንደሰጣቸው ነው፡፡ ገና ከታሪኩ መጀመሪያ እንደምንረዳው የአገልጋዮቹ ጌታ ምንም እንኳን እርሱ ለመንገድ ቢዘጋጅም ሀብቱ ግን በተዘጋ ቤት ውስጥ ተቆልፎበት እንዲቀመጥ አልፈለገም፡፡ በዚህም አገልጋዮቹን ጠርቶ ገንዘቡን በአደራ ተቀብለው «እንዲያተርፉበት» ማዘዙን እንደማስረጃ ልናቀርብ እንችላለን፡፡ ሆኖም ግን ማትረፍ በመፈለጉ ብቻ ገንዘቡን ያለአግባብ አልበተነም፡፡ ነገር ግን ለእርሱ ቀረቤታ የነበራቸውን አገልጋዮቹን ጠርቶ ያውም እንደየችሎታቸው መጠን ሓላፊነቱ ሳይከብዳቸው እንዲሠሩበት ገንዘቡን አከፋፈላቸው፡፡ ይህ ጌታ ቅንነትና ርኅራኄ የበዛለት እንደሆነ የሚያመላክተን ነገር አለ፡፡ ይኸውም ለአገልጋዮቹ ሓላፊነትን ቢሰጥም እንኳን ከእነርሱ ጋር በነበረው ቀረቤታ ማን ምን መሥራት ይችላል የሚለውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለእያንዳንዳቸው እንደ ሓላፊነት የመሸከም አቅማቸው አምስት ሁለት አንድ እያደረገ መስጠቱ ነው፡፡ ምናልባት ስስት ባልተላቀቀው ስሜት ለሚያስብ ሰው የዚህ ጌታ መክሊት አሰጣጥ አድልዎ ያለበት ሊመስለው ይችላል፡፡ ታሪኩን እስከ መጨረሻው ብንከታተለው ግን የሚያሳየን የባለ መክሊቱን ባለቤት ቅንነት ነው፡፡ ቀጥለን እንደምናነበው ይህ ጌታ ለአገልጋዮቹ አትርፉበት ብሎ መክሊቱን ሰጥቷቸው በሔደበት ሀገር አልቀረም፡፡ ይልቁንም እያንዳንዱ በተሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው እንደመጣ እናነባለን፡፡ ስለዚህ አገልጋዮቹ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩ እንደሚጠይቃቸው እያወቀ ከአቅማቸው በላይ የሆነ መክሊትን በመስጠት ምን ሠርተው የተሰጣቸውን መክሊት ያህል ማትረፍ እንደሚችሉ በማሰብ እንዲጨነቁ አልፈለገም፡፡ በተቃራኒው የምናየው ያለምንም ጭንቀት ከአእምሯቸው በላይ ሳይሆን ባላቸው ኃይል ተጠቅመው መሥራትና ማትረፍ የሚችሉትን ያህል መክሊት እንደሰጣቸው ነው፡፡ ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው ሲመጣ አምስት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ አምስት እንዲሁም ሁለት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ ሁለት መክሊት አትርፎ ጌታቸው ፊት እንደቆሙ ያ ጌታም በእነዚህ አገልጋዮቹ ታማኝነት ተደስቶ ወደ ደስታው እንዳስገባቸው እናያለን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ያ አንድ መክሊት ተቀብሎ የነበረው ምድርን ቆፍሮ ያተርፍባት ዘንድ የተሰጠችውን መክሊት እንደቀበረ ከዚህም አልፎ ምን አደረክባት ተብሎ ሲጠየቅ የአመጽ ንግግር እንደተናገረ በዚህ ከፊቱ ያዘነው ጌታውም ያን ክፉ አገልጋይ እንዲቀጣ እንዳደረገው አናነባለን፡፡ በዚህኛው ክፍል ከተጠቀሰው ታሪክ ሦስቱን አካላት ማለት የመክሊቱን ሰጪ ጌታ፣ በጎ የተባሉ አገልጋዮችና ክፉ እና ሰነፍ የተባለውን አገልጋይ በተናጥል እንመልከታቸው፡፡

 1. የአገልጋዮቹ ጌታ፡- ይህ ሰው ለገንዘቡ ጠንቃቃ ከመሆኑ ባሻገር በአገልጋዮቹ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው እናያለን፡፡ በክፉው አገልጋይ ላይ ባለመታዘዙ ምክንያት የፈረደበትን ፍርድ /ልቅሶና ጥርስ ማፏጨት ወዳለበት በውጪ ወዳለ ጨለማ አውጡት/ ስንመለከት የሚያሳየን የአገልጋዮቹን ጌታ ታላቅ ሥልጣን ነው፡፡ ምንም እንኳን ሥልጣኑ ጽኑ ቢሆንም ይህ ጌታ ፍርዱ ግን በእውነት ላይ የተመረኮዘ መሆኑን ደግሞ በድካማቸው ታግዘው በተሰጣቸው መክሊት ላተረፉት በጎ አገልጋዮች የሰጣቸውን ፍጹም ደስታ መጥቀስ ይቻላል፡፡

2. በጎ አገልጋዮች:- በአገልጋዮቹ ጌታ በጎ አገልጋዮች የተባሉት አምስት መክሊት የተቀበለውና ሁለት መክሊት የተቀበለው ናቸው፡፡ እዚህ ጋር ማስተዋል የሚገባው እነዚህ ሁለቱ አገልጋዮች በጎ አገልጋዮች ለመባል ያበቃቸው አስቀድመው ብዙ ወይንም የተሻለ ቁጥር ያለው መክሊት ለመቀበል መብቃታቸው አይደለም፡፡ ጉዳዩ የመክሊቱ ቁጥር ሳይሆን በተሰጣቸው መክሊት መጠን የሚገባቸውን ያህል ደክመው ማትረፍ መቻላቸው ነው፡፡ ወይንም ያ ባለ አንድ መክሊት አገልጋይ ከሁለቱ ያሳነሰው ከአንድ በላይ መክሊት መቀበል የማይችል መሆኑ ሳይሆን በዚያችው በአንዷ መክሊት እንኳን መሥራት አለመቻሉ ነው፡፡ 3. ክፉና ሰነፍ አገልጋይ:- ይህ ሰው የተጠቀሱ ሦስት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡ ሀ. የአገልጋዮቹ ጌታ ወደ መንገድ ሊሔድ በተዘጋጀበት ወቅት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደችሎታቸው ገንዘቡን ሲሰጣቸው አትርፈው እንዲቆዩት ነው፡፡ ከላይ እንደተነገጋገርነው እንደ አቅማቸው መስጠቱም አቅማቸው በሚፈቅደው የሥራ ደረጃ እንዲሰማሩ በማሰብ ነበር፡፡ ይህ ሰነፍ አገልጋይ ግን ያደረገው ከታዘዘበት ዓላማ በተቃራኒው መልኩ ነው፡፡ ሊሠራበት የሚገባውን መክሊት ቀበረው፡፡ ይህም ለጌታው ትዕዛዝ ያለውን ቸልተኝነት ያሳያል፡፡ ለ. ጌታው በመጣ ጊዜ አመጽ የተመላበት የሐሰት ንግግር ተናግሯል፡- ከሔደበት ቦታ ተመልሶ ጌታው በተሰጠው መክሊት ምን እንዳደረገ ሲጠይቀው «አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበሰብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንህ አውቃለሁ ስለፈራሁም ሔድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ፡፡» ሲል መለሰለት፡፡ ይህ ንግግር ከአመጽ ንግግርነቱ በተጨማሪ ውሸት አለበት፡፡ ምክንያቱም እርሱ እንዳለው ጌታው ካልዘራበት የሚያጭድ ካልበተነበት የሚሰበሰብ ጨካኝ ሰው ቢሆን ኖሮ ያደርግ የነበረው ምንም መክሊት ሳይሰጠው ከነትርፉ ሁለት መክሊቶችን ይጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ተጽፎ የምናነበው ትርፉን ከመጠየቅ በፊት አንድ መክሊት ሰጥቶት እንደበረ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አስቀድሞ ገንዘቡን ዘርቶ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ጌታ ዘርቷልና ማጨድ ይገባዋል፤ በትኗልና መሰብሰብም መብቱ ነው፡፡ ሐ. እርሱ መሥራት ሲሳነው እንኳን ዕድሉን ለሌሎች አልሰጠም፡- ይህ ሰው የተሰጠው መክሊት በትርፍ ሊመለስ እንደሚገባው ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ምክንያቱም ገና ሲቀበል ከጌታው የተቀበለው ትዕዛዝ ነውና፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን መውጣት መውረዱ ቢከብደውም ወጥተው ወርደው ማትረፍ ለሚችሉ ሰዎች አለመስጠቱ ተጨማሪ ጥፋቱ ነው፡፡ ይህን እንዳያደርግ ያሰረው ደግሞ ውስጡ የተቀረጸው የአመጽ መንፈስ ነው፡፡ ጌታው መጥቶ ስለ ትርፉ ሲጠይቀው የሚመልስለትን ረብ የለሽ ምክንያት እንደ መከላከያ አድርጎ ማሰቡ አእምሮው ሌላ አማራጭ እንዳያስብ የዘጋበት ይመስላል፡፡ የመጽሐፈ ቅዱስ መተርጉማን አባቶች የዚህን ምሳሌያዊ ታሪክ ምስጢር ሲያስተምሩ የአገልጋዮቹ ጌታ የፍጡራን ጌታ የሆነ የእግዚአብሔር ምሳሌ እንደሆነ እንዲሁም ሦስቱ አገልጋዮች በተለያየ ደረጃ ያሉ ምዕመናንን እንደሚወክሉ ያስተምራሉ፡፡ ከዚህ የወንጌል ክፍል ምን እንማራለን? ከተጠቀሰው ታሪክ የምንማራቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም አበይት የሆኑትን ሁለቱን እንመልከታቸው፡፡

 1. ለእያንዳንዳችን ከእግዚአብሔር የተሰጠ ስጦታ እንዳለ እንረዳበታለን እግዚአብሔር እያንዳንዳችን በሃይማኖት ሆነን የምናፈራውን ፍሬ ይፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን ከእኛ ፍሬን ቢፈልግም ያን ፍሬ ማፍራት የምንችልበትን ኃይል ግን የእግዚአብሔርን ልጅነት ካገኘንበት ከዕለተ ጥምቀት ጀምሮ እንደሚያስፈልገን መጠን እየሰጠን ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበልናቸው ስጦታዎች በቁጥር እጅግ ብዙ ቢሆኑም በአይነታቸው ግን ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው እያንዳንዱ ክርስቲያን ዳግመኛ በመወለድ ምስጢር ያገኘው የእግዚአብሔር ልጅነት ጸጋና ከልጅነት ጋር በተያያዘ የሚሰጡ ስጦታዎች ናቸው ፡፡ዮሐ.3-3 ሁለተኛው አይነት ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና እንደ ሰውየው አቅም ለተለያዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ማስፈፀሚያ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔር የሚሰጡ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ትንቢት መናገር ፣ በተለያዩ ልሳናት መናገር ፣ አጋንንትን ማስወጣት … የመሳሰሉት ከዚህኛው አይነት ስጦታ የሚመደቡ ናቸው፡፡ 1ኛ ቆሮ.12-4፡፡ በመጀመሪያውም ይሁን በሁለተኛው አይነት ስጦታ ተቀባዮች ዘንድ ግን ብዙ የሚያሳዝኑ ችግሮች አሉ፡፡ በዳግመኛ መወለድ ምሥጢር (በ40 ና 80 ቀን ጥምቀት) ስላገኘነው የልጅነት ጸጋ ጊዜ ሰጥቶ የሚያስብ ክርስቲያን ማግኘት በዚህ ዘመን በጣም አዳጋች ነው፡፡ በዓመት ውስጥ ክርስቲያንነቱ ለጥምቀት በዓልና ለመስቀል ደመራ ካልሆነ ትዝ የማይለው ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ ከቤተ ዘመድ አንድ ሰው ምናልባትም ራሱም ሊሆን ይችላል ነፍሱ ከሥጋው ካልተለየች ወደ ቤተ ክርስቲያን ደጅ ብቅ አይልም፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ የልጅነትን ጸጋ በመስጠቱ ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅሩን አሳይቶናል፡፡ ምክንያቱም ልጅነታችን ዋጋ ተከፍሎበታልና፡፡ እንዲሁ በቀላሉ አይደለም ልጆች የተባልነው፡፡ እኛ ልጅነትን እንድንቀበል አምላክ መከራን ተቀብሏል፡፡ የጥምቀታችን ውሃ የፈሰሰው በጦር ከተወጋው ከጌታ ጎን ነው ፡፡ ዮሐ.19-24፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ይሄንን ሁሉ ሲያመለክት ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ፡፡›› 1ኛ ዮሐ.3-1 ያለው፡፡ እኛ ልጆቹ እንሆን ዘንድ እግዚአብሔር ካሳየን የአባትነት ፍቅር በተጨማሪ ልጆቹ ስለመሆናችን የገባልንም ተስፋ ከአዕምሮ በላይ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ምዕመናን በላከው መልእክቱ ‹‹እንኪያስ እናንተ ልጆች ናችሁ እንጂ ባሮች አይደላችሁም፡፡ ልጆች ከሆናችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሾች ናችሁ፡፡›› ገላ.4-7 ስለሚጠብቀን ተስፋ ነግሮናል፡፡ ትልቁ ችግር ግን ተጠማቂው ሰው ይህን የልጅነት ክብር አለመረዳቱ ነው፡፡ የልጅነቴን ክብር ተረድቻለሁ እያለ የሚያወራውም ቢሆን የልጅነቱን መክሊት በልቡናው ውስጥ ቀብሮ አንድም ፍሬ ሳያፈራ ስለማንነቱ ለማውራት ቃላት ሲመርጥ ጊዜውን ያባክናል፡፡ አብዛኛው ግን የክርስትና እምነት ደጋፊ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅነት ሊገለጥ የሚገባው እንደ ሀገር ልጅነታችን በምናሳየው የደጋፊነት /የቲፎዞነት/ ስሜት አይደለም፡፡ ደጋፊነት በጊዜ ና በቦታ ለተወሰነ ያውም ኃላፊ ለሆነ ድርጊት ነው፡፡ ክርስትና ግን በማንኛውም ቦታ፣ ጊዜ የሚኖርበት የህይወት መስመር እንጂ የሚደገፍ ጊዜያዊ ድርጊት አይደለም፡፡ ስለዚህ በጣም ልንጠነቀቅበት የሚገባን የመጀመሪያው መክሊታችን ልጅነታችን መሆኑን መረዳት ያስፈልገናል፡፡በዚህም መክሊት እንድንሰራ የታዘዝናቸውን ምግባራት እንድናፈራ የሚጠበቅብንን ፍሬዎች ማፍራት አለብን፡፡ ያለበለዚያ መክሊቱን እንደቀበረው ሰው መሆናችን ነው፡፡

 2. እያንዳንዱ ስጦታ እንደሚያስጠይቅ እንረዳለን እግዚአብሔር ያለ አንድ አላማ ለሰዎች ኃላፊነትን የሚያሰከትል ስጦታ አልሰጠም አይሰጥምም፡፡ ማንም ከእግዚአብሔር የተቀበለ ሰው የተሰጠው ስጦታ ለሆነ አላማ ነውና ጥያቄ አለበት፡፡ ጠያቂው ደግሞ የስጦታው ባለቤት ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ መንጋውን እንዲጠብቁለት ሥልጣንና የተለያዩ የአገልግሎት ሰጦታዎችን እግዚአብሔር የሰጣቸው አሉ፡፡ዮሐ. 21-15 ፤ ገላ.1-15-16፡፡ ሆኖም ግን የተሰጣቸው ኃላፊነት የሚያስጨንቃቸው፣ ከልባቸው በእውነተኛ ትህትና የሚተጉ ያሉትን ያህል የሚያገለግሉበትን ስጦታ ከእግዚአብሔር መቀበላቸውን እንዲሁም የሚያስጠይቃቸው መሆኑን እስኪዘነጉ ድረስ መንገዳቸውን የሳቱ አሉ፡፡ በእግዚአብሔርና በሰዎች መሀከል እንደ ድልድይ ሆነው ያገለግሉበት ዘንድ በተሰጣቸው ሥልጣን እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ተግባር የሚፈፅሙ ሰዎች ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እንዲሁም ደግሞ ተሰባኪውን ወደ እግዚአብሔር ከመምራት ይልቅ የነሱ ደጋፊ፣ ስለክብራቸው ተሟጋች እንዲሆን በህዝቡ መሀከል ጎራ እንዲፈጥርና የጳውሎስ ነኝ የአጵሎስ ነኝ እንዲል የሚያደርጉት ሰባኪዎችም ሌሎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ማንም ይሁን ማን ግን ስለተሰጠው መክሊት ባለቤቱ ከፊቱ አቁሞ እንደሚጠይቀው መዘንጋት የለበትም፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አዲስ መጽሐፋዊ ጽሑፍ

July 16, 2010

              በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ከዚህ ቀጥሎ በተከታታይ በመጽሐፍ መልክ እየተዘጋጀ ጽሑፍ በድህረ ገጻችን ይቀርባል። የመጽሐፉ አላማ ከዚህ በታች በመግቢያው ላይ  እንደተገለጠው ሲሆን በወንጌልና በክርስትና ትምህርት ላይ የሚነሱ አንዳንድ ጥያቄዎችን በማንሳት ለማወያየትና ክፉውን ከመጥፎው እንድለይ እንዲረዳን ታስቦ በመዘጋጀት ላይ ያለ ነው። ማስተካከያ ወይም አስተያየት ካለዎት እንዲጽፉልን የተለመድ ጥያቄያችንን እናቀርባለን።

በክርስትና ላይ ግር ያለዎትን ወይም ጥያቄ የሆነብዎትን ይላኩልን የክርስቶስ ቃል ወንጌል መልስ አለው።   ጥያቄዎን ማወቃችን መጽሐፍትን ለማገላበጥ ይጠቅመናል። ለሌሎች ወንድሞችም መልስ እንዲያገኙ እየረዱ ነው።                                            

  የመጽሐፉን ሙሉ መግቢያ ለማንበብ Introduction

 So Many Questions for Many Years! Forward your dilemmas and questions to us,  Christ has suitable answers to you!

በመጽሐፍ መሳተፍ ለምትፈልጉም ድህረ ገጻችን ክፍት ነው። በአድራሻችን ላኩ።

 

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው? ክፍል ሰባት

April 27, 2010

ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዲሲ ኪዳን ሊቀ ካህን ነው፦

ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህን /ካህናት አለቃ / ነው። የተለዩ የእግዚአብሔር ካህናት ስላሉ የእነርሱ አለቃ መሆኑን ሲያመለክት ክርስቶስን ሊቀ ካህናት ይለዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህንነት እንዴት ነው ? የኢየሱስ ሊቀ ካህንነት እንደ ኦሪት ሊቃነ ካህናት ነውን ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለኢየሱስ ሊቀ ካህንነት ምን ይላል የሚለውን እንመለከታለን።
መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስን ሊቀ ካህነነት ከሌዋዊያን ሊቃነ ካህናትና ከሰላም ንጉስ ከመልከ ጼዴቅ ሊቀ ካህንነት ጋር አነጻጽሮ ይነግረናል።

የመልከ ጼዴቅና የኢየሱስ ክርስቶስ ካህንነት
-መልከ ጼዴቅ ፍጹም ጻድቅ የነበረ፤ ጻድቁ አብርሃም ከእርሱ የተባረከለት ካህን ነበር።ዕብ 7፤ 1-3፣ ዘፍ 14፤ 17-20 ኢየሱስ ክርስቶስም ፍጹም ጻድቅ ሁሉን የባረከ የሚባርክ ነው።
-መልከ ጸዴቅ ሹመቱ ለዘለዓለም ነው፤ የአይሁድ ሊቃነ ካህናት ሹመት የሚያልፍ የሚተካ ነበር ለምሳሌ ዘሁ 20፤ 22 ላይ እንደምናገኘው የአሮን ሊቀ ካህንነት ለልጁ ለአላዛር ሲሰጥ እናገኛለን። የመልከ ጸዴቅ ሊቀ ካህንነት ግን ለዘለዓለም ነበር። የኢየሱስ ክርስቶስም ሊቀ ካህንነት ለዘለዓለም ያለ የሚኖር ነው በዚህ ጊዜ ያልፋል አይባልም። ዕበ 7፤ 1-3፤መዝ 109፤ 4 ፡ ዕብ 5፤ 6
-መልከ ጸዴቅ ሹመቱን ከማንም አላገኘውም። ሌሎች ሊቃነ ካህናት በሰው ይሾሙ ነበር። መልከ ጸዴቅ ግን ሹመቱን ከእግዚአብሔር አግኝቶታል እንጂ ማንም አልሾመውም። ኢየሱስ ክርስቶስም ሹመቱ ከሰማይ ከአባቱ ዘንድ የሆነች ናት እንጂ ሰው ሾመው አይባልም።
-መልከ ጸዴቅ ያቀረበው መስዋዕት ህብስትና ጽዋ ነበር ዘፍ 14፤ 17-20 ኢየሱስ ክርስቶስም ለሐዲስ ኪዳን መስዋዕት ይሆነን ዘንድ ሰርቶ ያሳየን ስጋውንና ደሙን ነው።ማቴ 26፤ 57-65

መልከ ጸዴቅ የክርስቶስ ምሳሌ ነው። በመሆኑም መልከ ጸዴቅን ከክርስቶስ ጋር አነጻጽሮ ሐዋርያው ብዙ ተናግሯል። በአንጻሩ የአይሁድ ሊቃነ ካህናት ድካም ያለባቸው በመሆናቸው በአሉታዊ ጎኑ ከክርስቶስ ሊቀ ካህንነት ጋር አነጻጽሮ እንደሚከተለው ያቀርባቸዋል።

የኦሪት /የአይሁድ ሊቃነ ካህናት እና የኢየሱስ ሊቀ ካህንነት፡

የኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህንነት ዘለዓለማዊ ነው ነገር ግን አንድ ጊዜ ራሱን መስዋዕት አድርጎ ባቀረበ ጊዜ የተፈጸመ ነው። መስዋዕቱ ዛሬ ያው ነው ለሚያምኑበት ሁሉ ያለ የማያልፍ ነው ሐዋርያው የኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህንነት ከአይሁድ ሊቀ ካህንነት የተለየ እንደሆነ ሲናገር ዕብ 7፤ 27 እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።

-የኦሪት ሊቃነ ካህናት ያቀርቡ የነበረው የእንስሳትን ደም ነበር ኢየሱስ ግን ያቀረበው የራሱን ደም ነው

የኦሪት ሊቃነ ካህናት ወደ እግዚአብሔር እየለመኑ ሐጢያትን ያስተሰርዩ ነበር። በተለይም በአመት አንድ ጊዜ ካህኑ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ደም ይዞ በመግባት ስለህዝቡና ስለራሱ ጸሎት ያቀርባል። ዘጸ 30፤ 10 ይህንን አንዱ ሊቀ ካህን ሲሞት በሌላው እየተካ መስዋዕትን ያቀርባል። ዕብ 9፡ 7 በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፥ እርሱም ሰለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ስሕተት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም፤
ለዚህ ነው ሐዋርያው ዕብ 9፤ 25 12 የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። ያለው።በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎች ወይም በጥጆች ደም አይደለም። የሌላውን ደም ሳይሆን የራሱን ደም ነው ያቀረበው። በእንስሳት ደም አይደለም ዓለም የዳነው በእርሱ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም እንጂ።

-የኦሪት ሊቃነ ካህናት በልመናና በእንስሳት ደም ሐጢያትን ያስተሰርዩ ነበር ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ በደሙ በራሱ ነው ሐጢያትን ያስተሰረየው
ዕብ 1፤ 33 እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤

-የኦሪት ሊቃነ ካህናት ሞትና እርጂና ነበረባቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ለሊቀ ካህንነቱ ሽረት /መለወጥ / የለበትም
የኦሪት ሊቃነ ካህናት ድካም ነበረባቸው ሐጢያት ይሰራሉ በሌላ በኩል ሰዎች ስለሆኑ ለዘለዓለም መኖር አይችሉም። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እርሱ ከሐጢያት የራቀ ፍጹም ነው እርሱም ለዘለዓለም የሚኖር የማያልፍ ነው። ዕብ 7፡ 28 ሕጉ ድካም ያላቸውን ሰዎች ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣ የመሐላው ቃል ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ይሾማል።

-የኦሪት ሊቃነ ካህናት በእየጊዜው እግዚአብሔር ይቅር እንዲል መለመን ነበረባቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አንድ ጊዜ ባደረገው የመስቀል ስራ /ሊቀ ካህንነት / አዳነን
ዕብ 9፤ 26-27 ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ያደረገው የማዳን ስራ እስከዘለዓለም በስሙ ለሚያምኑ ሁሉ የተከፈለ ዋጋ ነው። ዛሬ በቤተ የሚሰዋው መስዋዕት በእለተ አርብ ከፈሰሰው ደሙና ከተቆረሰው ስጋው ጋር አንድ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክነቱ ፤ በሊቀ ካህንነቱ ዛሬም ከሞተ ስራችን ነጻ ያደርገናል። ደሙ ከሐጢያት ሁሉ የነጻልና። 1ኛ ዮሐ 2፤ 1 ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።

ቅዱሳን እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ

March 31, 2010

በዚህ ርዕስ የቅዱሳንን ማንነትና ክርስቶስ እርሱን እንዲመስሉ የሰጣቸውን ስልጣን እንመለከታለን። እግዚአብሔር ለስጦታው ወደር ለቸርነቱም ቁጥር የለውምና በእርሱ የሚያምኑ እርሱን እንመስሉ ስለጣን ሰጥቷል። ይልቁን በስጋ የተገለጠው አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ  እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፥ /ዮሐ 14፤12/ ብሎ እንዳስተማረ በክርስቶስ እስከሞት ድረስ ያመኑ ቅዱሳን እርሱን እንዲመስሉ አድርጓል። በመሆኑም ከዚህ ቀጥለን የቅዱሳንን ማንነትና በምን ክርስቶስን እንደሚመስሉ በተወሰነ ደረጃ እንመለከታለን።
ኢየሱስ ክርስቶስ የአማልክት አምላክ የጌቶች ጌታ የነገስታትም ንጉስ ነው።/ሮሜ 9፤5 ፤1ኛ ዮሐ 5፤19 ራዕ 17፤14 / ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለማትን የፈጠረ እግዚአብሔር ነው።/ዮሐ 1፤1 ቆላ 1፤ 16-17/ እርሱ ፈጣሪ ቢሆንም አዳም በበደለው በደል ምክነያት ሞት ስለተፈረደበት አዳምን ከሞት ነጻ ለማድረግ ከሰማያት ወርዶ ክድንግል ተወልዶ እንደ እኛ ሰው ሆኖ በመካከላችን ተመላልሶ አርአያውን ትቶልን ሄዷል። በዚህም ከእርሱ እንድንማር አስረድቶናል። ከእኔም ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝና። ማቴ 11፡ 39 እንዲሁም ቅዱስ ጴጥሮስ ክርስቶስ ደግሞ እርሱን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለእናንተ መከራን ተቀብሏልና። 1ኛ ጴጥ 2፤ 21 ይላል በዚህም ኢየሱስ ክርስቶስን እንደምሳሌ አድርገን እርሱን እንድንመስል ለማስረዳት ነው። ማነኛውም ክርስቲያን እርሱን ሊከተል እንደሚገባውና ከእርሱ ህይወት መማር እንደሚገባን ቤተ ክርስቲያን ታስተምረናለች።ቅዱስ ጳውሎስም እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተም እኔን ምሰሉ ይላል።
ቅዱሳን ኢየሱስን እንዲመስሉ እግዚአብሔር መወሰኑን ሲያስረዳ ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው።ሮሜ 8፤28-30 በዚህ ጥቅስ ላይ ቅዱሳንን አስቀድሞ እግዚአብሔር እንደጠራቸው የእግዚአብሔርልን ልጂ ኢየሱስ ክርስቶስን ይመስሉ ዘንድ እንደወሰነ ይናገራል። የልጁን መልክ ሲል እኛ የምናውቀውን ገጽ ማለት አይደለም የኢየሱስን ቅድስና ንጽሕና ክብር እንዲከተሉ ስራውን እንዲከተሉ እግዚአብሔር ወስኖላቸዋል። እንዲያውም እግዚአብሔር የልጁን መልክ የመሰሉ ቅዱሳንን ራሱ እንዳከበራቸው ሲገልጽ ያጸደቃቸውን ደግሞ አከበራቸው ይላል። ቅዱሳንን ያከበረ ራሱ እግዚአብሔር ነውና።
ቅዱሳን እንማን ናቸው?
ቅዱስ ማለትም የተለየ ማለት ሲሆን ቅዱሳን ሲሆን የተለዩ የሚለውን ያመለክታል። ቅዱሳን የተለዩ ናቸው ሲባልም ከዚህ አለም ርኩሰትና ሐጢያት የተለዩ ለእግዚአብሔር ክብር ራሳቸውን ያዘጋጁ ማለት ነው። ቅዱሳን ከራሳቸው ይልቅ ለእግዚአብሔር የኖሩ፤ አለምንና በእርሷ ያለውን የናቁ እነርሱም በአለም የተናቁ ፤ስለወገኖቻቸው በሐጢያት መውደቅ የሚያዝኑ ስለክርስቶስ መንግስት የመሰከሩ ናቸው።

ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳን ብላ የምትጠራቸው ቅዱሳን ሰዎች እግዚብሔርን በተለያየ መንገድ ሊያክብሩት ቢችሉም በአጠቃላይ ግን በሚከተሉት መልኩ ልንመድባቸው እንችላለን።

ቅዱሳን ሰማዕታት፡ ሰማዕት ማለት ምስክር ማለት ሲሆን ምስክርነታቸውን ለእግዚአብሔር ነው።እስከ ደም ጠብታ ድረስ ለእግዚአብሔር ሲሉ ራሳቸውን መስዋዕት ያደረጉና እውነትን የመሰከሩ ናቸው። የሰይፍ መሳል የእሳት መጋል አውነትን ከመመስከርና ስለእግዚአብሔር ሐያልነት ከመናገር ያላስቆማቸው ናቸው። ህይወታቸውን እስከመስጠትና እስከ መገደል ከቦታ ቦታ እስከመሰደድ ድረስ እግዚአብሔርን በህይወታቸው ያከበሩትን ቅዱሳንን ሰማዕታት እንላቸዋለን። እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የህይወትን አክሊክ አቀናጂሀለሁ ያለውን የክርስቶስን ቃል ይዘው የታመኑ ናቸው።/ ራዕ 2፤10/ ከነቢያት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ስለአንዲቱ እምነታቸው ስለእግዚአብሔር ክብር መከራ የሚቀበሉት ሁሉ ሰማዕታት እንላቸዋለን።

ቅዱሳን ጻድቃን፡ ጻድቃን ማለት እውነተኞች ማለት ነው። እነዚህም ሐዋርያው ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ። እንዳለው /ዕብ 11፤38/ ከዚህ ዓለም ራሳቸውን ለይተው በጾምና በጸሎት ራሳቸውን ጠምደው እግዚአብሔር ሲያገለግሉ የኖሩ አባቶችና እናቶች ጻድቃን ይባላሉ። እነደ አብርሃምና እንደ ኢዮብም በዓለም እየኖሩ እግዚአብሔርን በህይወታቸው ሙሉ ያከበሩ ቅዱሳንም ጻድቃን ይባላሉ።

ቅዱሳን ሊቃውንት፡ ቅዱሳን ሊቃውንት የምንላቸው በህይወታቸውና በኑሯቸው እየመሰከሩ የክርስቶስን የክብር ወንጌል ለዓለም ያስተዋወቁ ናቸው እኒሁም ከሐዋርያት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ የሚነሱ በእውነተኛው የክርስትና ትምህርት ላይ የታነጹ የሚያንጹም ናቸው። ተከራክረው መናፍቃንን የሚረቱ ከሐዲያንን የሚያሳምኑ ከእውቀታቸው ጋር ህይወታቸውን ለእግዚአብሔር ያስገዙትን ሊቃውንት እንላቸዋለን።
ታዲያ ቅዱሳን እንዴት ኢየሱስን ይመስሉታል?
ቅዱሳን እግዚአብሔር የሆነውን እርሱን ኢየሱስን ይመስላሉ ስንል ቅዱሳን አምላክ ናቸው ማለት አይደለም። ቅዱሳን እግዚአብሔር ራሱ ስላከበራቸው ከእግዚአብሔር የተነሳ የተከበሩ ናቸው። ስለጣናቸውን ክብራቸውን ጸጋቸውን ሁሉ ከእግዚአብሔር ያገኙት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በራሱ በባህርይው የከበረ ነው። እርሱ ፈጣሪ ነው አርሱ አምላክም ነው እርሱ አክባሪ ነው የሚያከብረው አይፈልግም ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ሆኗልና።
ቅዱሳን እርሱ በሰጣቸው ጸጋ መሰረት ኢየሱስ ክርስቶስን ይመስላሉ። ታዲያ እንዴት ይመስሉታል ማለታችን አይቀርም። ጌታችን ሲያስተምር በዮሐ 8፤12 እኔ የአለም ብርሃን ነኝ ይላል እንዲሁም ማቴ 5፡14 ላይ ቅዱሳኑን እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። ይላቸዋል። እግዚአብሔር ቅዱሳንን እንዴት እንደሚያከበራቸውና ጸጋውን እንዴት እንዳበዛላቸው የሚያሳይ ነው። እርሱን ብርሃኑን ስለተከተሉ እነርሱ ደግሞ ለዓለም ብርሃን ናቸውና። በመሆኑም ከዚህ ቀጥለን ቅዱሳን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚመስሉበትን አንዳንድ ጉዳዮች እንመለከታለን።
1. ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝ ፈዋሽ ነው ቅዱሳንም የመፈወስ ጸጋ ሰጥቷቸዋል
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መድሓኒት ነው። እግዚአብሔር ፈዋሽ ስለሆነ የሚሳነውም ስለሌለ እርሱ ከማናቸውም ነገር ማዳን ይችላል። ስለኢየሱስ ክርስቶስ ፈዋሽነት መጽሐፍ ቅዱስ በጥልቀት ይናገራል። ከሞተ አራት ቀን የሆነውን አልአዛርን ከመቃብር አስነስቶታል (የሐ 11)፤ የሞተችዋን የኢያንሬዎስን ልጂ አስነስቷል፤ ሲወለድ ጀምሮ አይን ያልነበረውን ሰው አይን ሰርቶለታል /ዮሐ 9/፤ ሁለቱን እውሮችም አይናቸውን አብርቷል /ማቴ 9/ ። ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህም አልፎ ጨርቁ እንኳን ለሚያምኑበት ይፈውስ ነበር። አስራ ሁለት አመት ደም ይፈሳት የነበረችዋ በሽተኛ ሴት ልብሱን የነካሁ እንደሆነ እፈወሳለሁ ብላ በማመኗ ብቻ ልብሱን ነክታ ተፈውሳለችና።

ቅዱሳን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚከተሉ እግዚአብሔርን የሚያከብሩ ስለሆኑ ቅዱሳን የመፈወስ ስለጣንን ከኢየሱስ ክርስቶስ ተቀብለዋል። አስራ ሁለቱንም ጠርቶ በእርኩሳን አጋንንት ላይ ስልጣን ሰጣቸው እንዲል ። ሐዋርያትም ይሁኑ ነቢያት ከዚያም በሗላ የተነሱ ቅዱሳን አምላካቸውን ክርስቶስን ከመሰሉበት አንዱ ነገር በእርኩሳት መናፍስት ላይ ስልጣን ስላላቸው ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ ሀይልና ስልጣን አጋንንትን እንዳስወጣ ሁሉ ቅዱሳን ደግሞ የእርሱን ስም መከታ አድርገው በስላሴ ስም፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፤ በእግዚአብሔር ስም ፤ በሐዋርያት ስልጣን አጋንንትን ያስወጣሉ። ለምሳሌ ያክል በሐዋ3፤2 ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ፥ ሰዎች ተሸክመው መልካም በሚሉአት በመቅደስ ደጅ በየቀኑ ያስቀምጡት የነበሩ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ አንካሳ የሆነ አንድ ሰው ነበረ። ይህንን ሰው ሐዋርያቱ ቅዱስ ጴጥሮስና ዮሐንስ ፈውሰውታል።ሐዋ 3፤8 ተመሳሳይ የፈውስ ታሪክ በሐዋ 9፤34 ላይም እናገኛለን ሽባውን ቅዱስ ጴጥሮስ ፈውሶታልና።
ቅዱሳን በመፈወስ ብቻ ሳይሆን ሙታንንም ያስነሳሉ፦ ቅዱስ ጴጥሮስ ከሞተች በሗላ ጣቢታን አስነስቷል /ሐዋ 9፤41/ ቅዱስ ጳውሎስም እንዲሁ ከፎቅ ላይ ወድቆ የሞተውን ክርስቲያን አድኖታል። ሐዋ 20፤9 እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ድንቅ ታምራት ያደርግ ነበርና።
ቅዱሳን እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ ጥላቸውና ልብሳቸው ሳይቀር ይፈውሳል። የቅዱሳን ነገር ሲነሳ የማይዋጥላቸው ሰዎች ቢኖሩም እግዚአብሔር ሁለንተናቸውን ስላከበረው ቅዱሳን ነገራቸው ሁሉ ይፈውሳል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልብስ እንፈወሰ ሁሉ የቅዱስ ጳውሎስም ልብሱ ይፈውስ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል። ሐዋ 19፤11 እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር። የቅዱስ ጴጥሮስም ጥላው ፈዋሽ ነበር። ሐዋ 5፤15 ስለዚህም ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከእነርሱ አንዱን ይጋርድ ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋና በወሰካ ያኖሩአቸው ነበር።

 
2. ኢየሱስ ክርስቶስ አለምን ከራሱ ጋር አስታርቋል ቅዱሳን ደግሞ ያማልዳሉ
ምልጃ ማለት አንድን አካል ወክሎ በሌላ አካል ፊት ልመናን ማቅረብ ማለት ነው። በመንፈሳዊው አለም ምልጃ ለአንድ ሰው ወይም ሀገር ወደ እግዚአብሔር ልመናን ማቅረብ ነው። አንድ ሰው ስለሌላ ሰው ወደ እግዚአብሔር የሚያደርገው ልመናና ጸሎት ምልጃ ይባለል።

የተወደዳችሁ ምዕመናን ሆይ እንግዲህ እግዚአብሔር ያከበረውን ማን ይከሰዋል እግዚአብሔርስ እንዲፈውሱ ስልጣንን ከሰጣቸው ማን ሊቃወም ይችላል? ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሆን አናውቅምን?
ዛሬ አንዳንዶች ይህንን ፈውስ ለማስመሰል ጸጋው ሳይሰጣቸው የፈወሱ ለመምሰል ሲጣጣሩ እንመለከታለን። የሐሰት በሽተኞች አዘጋጂተው የሐሰት ክራንች አስይዘው በሐሰት ፈወስን የሚሉ የዘመኑ ሐሰተኛ ነቢያትን ማየት የተለመደ ሆኗል እኛ ግን እውነቱን ከሐሰቱ እንድንለይ እግዚአብሔር ማስጠንቀቂያ ስለሰጠን ከሐሰተኞች ማታለል እንጠበቅ። እግዚአብሔር ጸጋ የሰጣቸውን እውነተኞችን ቅዱስንም እናክብር።

ልመናን የሚቀበል ሐጢያትን የሚያስተሰርይ እግዚአብሔር ስለሆነ ምልጃ የሚቀርበው ወደ እግዚአብሔር ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይግባውና በስጋው ወራት በተመላለሰበት ጊዜ ለእኛ አርአያ ይሆነን ዘንድ ስለደቀ መዛሙርቱ እንዲሁም ስለጠላቶቹ ይጸልይ ነበር። የሐ 17፤1-26 ሉቃ 23፤34 ክርስቶስ ምንም እንኳን ራሱ እግዚአብሔር ቢሆንም እና ራሱ የመማርም ሆነ የመፍረድ ስልጣን ቢኖረውም ለእኛ አርአያ ይሆን ዘንድ ሲለምን እናየዋልን። ይህም እኛ እርስ በእርሳችን አንዱ ስለአንዱ እንዲለምንና እንዲማልድ ያስተምረን ዘንድ ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋው ወራት ቢጸልይም ቢለምንም እንኳን ከሞተና ከተነሳ በሗላ ልመናን ምልጃን የሚያደርጉ ቅዱሳን እንደሆኑ እንጂ ራሱ እንደማይለምን በአጭር ቃል አስቀምጧል።
ዮሐ 16፤26 በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም፤ በዚህም እነርሱ እንደሚለምኑ እንጂ እርሱ አብን በስጋው ወራት እንደነበረው ሁኔታ እንደማይለምን ተናግሯል። የኢየሱስ ክርስቶስን ትዕዛዝ ይዘውም ቅዱሳን ሲያማልዱ ኖረዋል አሁንም ያማልዳሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ ቅዱሳን እንደሚያማልዱ በግልጽ አስቀምጧል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቶስ አለምን ከራሱና ከአባቱ ጋር ካስታረቀ በሗላ በአሁኑ ጊዜ ቅዱሳን እንደሚያስታርቁ /እንደሚያማልዱ/ ሲናገር።
2ኛ ቆሮ 5፤18 ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ የማስታረቅ አገልግሎት የሰጠን ሲል ቅዱሳን አስታራቂዎች /አማላጆች/ መሆናቸውን ለመጥቀስ ነው። ቀጥሎም በእኛም የማስታረቅን ቃል አኖረ ብሎ ይናገራል። ቅዱሳን የማስታረቅን የማማለድን ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተቀብለዋልና። እንዲሁም ይህ ሐዋርያ ስለ ቅዱሳን ሲናገር ራሳቸውም ስለ እናንተ ሲያማልዱ፥ በእናንተ ላይ ከሚሆነው ከሚበልጠው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ይናፍቁአችኋል። 1ኛ ቆሮ 9፤14 ለምዕመናኑ የተመረጡ ቅዱሳን እንደሚማልዱ ሲያመለክት ነው።
2.1. የምልጃ መስራች ማን ነው?
አንዳንድ ሰዎች ምልጃን ሰዎች የፈጠሩት ይመስላቸዋል ነገር ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ምልጃን ለሰው ልጆች ያስተዋወቀ ራሱ እግዚአብሔር ነው። የአብርሃምን ሚስት ሳራን ከአብርሃም ለይቶ ለመገናኘት የፈለገውን ንጉሱን አቤሜሌክን እግዚአብሔር ከተቆጣው በሗላ እንድምርህ ይቅርታ እንዳደርግልህ አብርሃም ይጸልይልህ /ያማልድህ/ ብሎታል። ዘጽ 20፤7 አሁንም የሰውዬውን ሚስት መልስ፤ ነቢይ ነውና፥ ስለ አንተም ይጸልያል፥ ትድናለህም። እግዚአብሔር ራሱ አንተ ጸልይ እምርሃለሁ አላለውም እርሱ ይጸልይልህ አለው እንጂ። ሶስቱ የኢዮብ ወዳጆች ኢዮብን የሚያሰቀይም ነገር በተናገሩና እግዚአብሔርን ባሳዘኑ ጊዜ ራሱ እግዚአብሔር ወደ ኢዮብ ሂዱና ኢዮብ ስለእናንተ ያማልዳችሁ ሲላቸው እናያለን። ኢዮ 42፡8 ወደ ባሪያዬ ወደ ኢዮብ ዘንድ ሂዱ፥ የሚቃጠልንም መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ አሳርጉ፤ ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፥ እኔም እንደ ስንፍናችሁ እንዳላደርግባችሁ ፊቱን እቀበላለሁ።
እንግዲህ ከዚህ የምንመለከተው እግዚአብሔር ምንም እንኳን ማንንም የሚሰማ ቢሆንም እንኳን ምልጃ ደግሞ የእርሱ ፈቃድና ትዕዛዝ እንሆነና ቅዱሳን እንዲያማልዱ ፈቃድና ትዕዛዝ የሰጠ እርሱ መሆኑን አስረድቶናል።
ምልጃም ያስፈለገበት ዋናው ምክነያት እግዚአብሔር ከሐጢያተኞች ይልቅ የቅዱሳንን ስለሚሰማና የቅዱሳንን ልመና ለመፈጸም ደስ ስለሚለው ነው። 1ኛ ጰጥ 3፤12 የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፥ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው።
2.2. የቅዱሳን ምልጃ በአጠቃላይ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠ ቢሆንም የሚከተሉትን ጥቅሶች እንመልከት
እግዚአብሔር በአብርሃም ምልጃ አቤሜሌክን እንደፈወሰው ዘፍ 20፡ 17፤ አብርሃምም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም አቢሜሌክን ሚስቱንም ባሪያዎቹንም ፈወሳቸው፥ እነርሱም ወለዱ፤ አብርሃም ስለሰዶምና ገሞራ በእግዚአብሔር ፊት ማልዷል። ዘፍ 18፤20-33
ነቢዩ ኤልያስ አማልዶ የህጻኑን ነፍስ አስመልሷል።1ኛ ነገ 17፤17-24 እንዲሁም ኤልያስ አማልዶ ለሶስት አመት አልዘንብ ያለው ዝናብ እንዲዘንብ አድርጓል። 1ኛ ነገ 18፤30 ኤልሳዕ በምልጃው የሞተውን ልጂ አስነስቷል። 2ኛ ነገ 4፤18-36።
ኢዮብ እግዚአብሔር የልጆቹን ሐጢያት ይቅር ይል ዘንድ በእየእለቱ ሲማልድ እንመለከተዋለን /ኢዮ 1፤5/ ኢዮብ ለጓደኞቹ እንዲማልድ እግዚአብሔር እንዳዘዘና ኢዮብ እንደማለደም መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ኢዮ 42፡8።
ሙሴ የህዝብ መሪና ነቢይ ስለነበረ ጊዜውን በአጠቃላይ ያሳለፈው ለእስራኤል በመማለድ ነው። ሙሴ ለፈርኦን አማልዷል /ዘጸ 8፤8-15 ዘጸ 8፤25-31/
ሙሴ እስራኤል ጣኦት በማምለካቸው ምክነያት እግዚእብሔር ሊያጠፋቸው ስለተቆጣ ሙሴ እንዳይጠፉ አማልዶ አስምሯቸዋል/ዘጸ 32፤1-15/ ሙሴ እህቱና ማርያምና ወንድሙ አሮን ኢትዮጲያዊቷን በማግባቱ በተቆጡ ጊዜ እህቱን እግዚአብሔር በለምጽ ስለመታት አማልዶ አድኗታል /ዘሁ 12፤1-7/
ቀዳሚ ሰማዕት እስጢፋኖስ ስለገደሉት ሰዎች ተንበርክኮም። ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ እየጸለየ ብሎ ሲያማልድ እናየዋለን።/ሐዋ 7፤60/።
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምልጃ እንዲደረግም ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀመዝሙሩ ይነግረው ነበር።ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። 1ኛ ጢሞ 2፤1-2
የሰዎች ልጆች ልመናን ማቅረብ የሚችሉት በህይወት እያሉ ብቻ አይደለም ከዚህ ዓለም ካለፉም በሗላም በሰማይ ሆነው ልመናን ማቅረብ ይችላሉ። ለምሳሌ ጌታችን በሉቃ 16፤20-31 እንዳስተማረው ሐጢያተኛው ነዊየ በምድር ስላሉ ስለሐጢያተኞች ወንድሞቹና ወገኖቹ ሲማልድ እናየዋለን። ከዚህ የምንረዳው እንኳን ቅዱሳን ሐጢያተኞች ከሞቱ በሗላም ሳይቀር ለወገኖቻቸው ምልጃን እንደሚያቀርቡ ነው። ሆኖም እግዚአብሔር የሐጢያተኞችን ምልጃ አይቀበልም በህይወታቸው እርሱን አላገለገሉምና። እንዲሁም በራዕ 6፤10 ላይ ቅዱሳኑ ወደ እግዚአብሔር ልመናን ሲያቀርቡ እንመለከታለን። እግዚአብሔር የህያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ ስላልሆነ ቅዱሳን በስጋ ቢሞቱ እንኳን ከዚህ አለም ተሰናበቱ እንጂ በእግዚአብሔር ዘንድ ህያዋን ናቸው። ለዚህ ነው ጌታችን ሲያስተምር በማቴ 22፤31-32እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። አብርሃም፤ ይስሃቅና ያዕቆብ በስጋ ከሞቱ በሗላ ሳይቀር ጌታ ህያዋን ይላቸዋል። እነርሱ ከእግዚአብሔር ጋር ህይወታቸውን ያሳለፉ በመሆናቸው ህያዋን ይባለሉና። አማላጂነታቸው ከእኛ ጋር ትሁን። አሜን።

3. ኢየሱሰ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ ነው ቅዱሳንም የጸጋ አማልክት ይባላሉ
ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይግባውና ምንም እንኳን ሰዎች በሚገባ ባይረዱትም እርሱ አምላክ ነው። እንዲያውም አይሁድ ሞት እንደፈረድበት ካስቀመጧቸው ክሶች ውስጥ ዋናው አንተ ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ታደርጋለህ የሚል ነበር።ዮሐ 10፤33 አይሁድም። ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ስለመሰላቸው አምላክነቱን በሚገባ ለመረዳት አልቻሉም። እርሱ በደከመው ስጋ የባርያን ምሳሌ ይዞ መጥቷልና። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ ፊሊ 8፤6-7 እርሱ ራሱን ዝቅ አድርጎ በመምጣቱ ሰዎች አምላክነቱን መረዳት ባይችሉም እርሱን አምላክ ከመሆን አላገደውም። ዛሬም እርሱ በደካማ ስጋ ተገልጦ ያደረጋቸውን ነገሮች ይዘው ሰዎች ኢየሱስ ፍጡር ነው ቢሉ ፍጡር ሊሆን አይችልም እርሱ ፈጣሪ ነውና። እርሱ አማላጂ ነው ቢሉት ሊሆን አይችልም እርሱ ፈራጂ ነውና። የሚያጸድቅም መኮነንም የሚችል እርሱ ነውና።2ኛ ጢሞ 4፡ 1 ምንም እንኳን የማያምኑ ሰዎች አምላክ አይደለም ቢሉት መጽሐፍ ቅዱስ ግን የክርስቶስን አምላክነት ይገልጣል። ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ 9፤ 5 እርሱ ከሁሉ በላይ ሆኖ የተባረከ አምላክ ነው።ሲል ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ በ1ኛ ዮሐ 5፤ 21 እርሱ እውነተኛና የተባረከ አምላክ ነው እንዲሁም ቶማስ በዮሐ 20፤ 8 ቶማስም ጌታየ አምላኬ ብሎ መለሰለት እንዲሁም ቅዱስ ጴጥሮስ 2ኛ ጴጥ 1፤ 1 በአምላካችንና በመድሓኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማለት የጌታችንን አምላክነት ገልጠዋል።ነቢዩ ዳዊት ገና ክርስቶስ ሳይወለድ እርሱን አምላክ እንዳለው ሐዋርያው ሲጠቅስ በዕብ 1፤ 11 ስለ ልጁም አምላክ ሆይ ዙፋንህ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የጸና ነው።
እንግዲህ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ ሁሉ ቅዱሳንን ደግሞ እርሱ ራሱ የጸጋ አማልክት ብሎ ሾሟቸዋል። እግዚአብሔር ራሱነው ቅዱሳንን አማልክት ያላቸው። በመዝ 82፤1 እግዚአብሔር በአማልክት ማኅበር ቆመ፥ በአማልክትም መካከል ይፈርዳል። በአማልክት መካከል ሲል ሌሎች አምላኮች አሉ ማለት ሳይሆን ቅዱሳንን ነው አማልክት ያላቸው። እንዲሁም ቁጥር 6 ላይ 6 እኔ ግን። አማልክት ናችሁ፥ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ፤ በዚህም መሰረት አማልክት የሚለው ቅዱሳንን ነው። ይህንን ኢየሱስ ክርስቶስ ጠቅሶ ተናገግሯል በዮሐ 10፤34-35 ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። እኔ። አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን?መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥ በዚህም የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸው ከእግዚአብሔር ጋር የተነጋገሩ ቅዱሳን አማልክት እንደተባሉ ያስረዳል።
እግዚአብሔር ነቢዩ ሙሴን በፈርኦን ላይ አምላክ አድርጎ እንደ ሾመው ሲናገር ዘጸ 7፤1 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። እይ፥ እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል። በዚህም በፈርኦን ላይ ስልጣን ኑሮት ያንን ሁሉ ታምር አድርጓል።
ወገኖቼ ሆይ ለቅዱሳን እግዚአብሔር የሰጣቸው ክብር ምነኛ ድንቅ ነው። ዛሬ ሰዎች የቅዱሳን ክብር ሊያቃልሉ ቢፈልጉም አግዚአብሔር ግን በሚሰጠው ጸጋ የማይቆጭ ነው። እርሱን ላገለገሉት እንደልቡም ለተገዙለት ቅዱሳን እግዚአብሔር ምን ያክል ክብር እንዲሚሰጥ እናያለን ቅዱሳንን አማልክ አድርጎ ሲሾም ተመልክተናልና።
4. ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን አዋቂ ነው ቅዱሳንም እግዚአብሔር በሰጣቸው ጸጋ የተሰወረን ነገር ያውቃሉ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በባህርይው ሁሉን ያውቃል። አምላክ ስለሆነ የሚሰወረው አንዳች የለም በእርሱ ዘንድ የራሳችን ጸጉር እንኳን ሳይቀር ይታወቃል። ጌታ ልብንና ኩላሊትን ይመረምራል አዕምሮ ያመላለሰውን ያውቃል።ራዕ 2፤23 አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ኵላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ። እንዲሁም በዮሐ 2፤24-25 ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፤ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና። ይላል። በዚህም ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን አዋቂ እንደሆነ እንረዳለን።
ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን ይመስሉ ዘንድ ለቅዱሳን ክብርን ሰጥቷቸዋልና። ለዚህም ቅዱሳን በሰው ልብ ያለውን ሳይቀር በመንፈስ ቅዱሰ ተረድተው ያውቁ እንደነበር እንረዳለን። ቅዱስ ጴጥሮስ ሐናኒያና ሰጲራ እቤታቸው ሆነው የተነጋገሩትን ሚስጢር ማንም ሳይነግረው አውቆታል። ሐዋ 5፤1-11 እንዲሁም ቅዱሱ የእግዚአብሔር ሰው ኤልሳ የሶሪያ ንጉስ የሚሰራውን ስራ እስራኤል ውስጥ በአንዲት ጎጆ ውስጥ ሆኖ ማወቅ ይችል ነበር።2ኛ ነገ 6፤12 ከባሪያዎቹም አንዱ። ጌታዬ ሆይ፥ እንዲህ እኮ አይደለም፤ ነገር ግን በእልፍኝህ ውስጥ ሆነህ የምትናገረውን በእስራኤል ዘንድ ያለ ነቢይ ኤልሳዕ ለእስራኤል ንጉሥ ይነግረዋል አለ። እግዚአብሔር መንፈሱን ስለሰጣቸው ቅዱሳን በሰው ልብ የማይታሰበውን ያውቃሉ። ቅዱሳን እውቀታቸው ከመንፈስ ቅዱስ ነው። ለዚህም ነው አባቶቻችን የእመቤታችን ልቦና እንደ አምላክ ልብ ነው ብለው የሚናገሩት እርሷ ጸጋን የተመላች ስለሆነች እውቀትን የሚገልጥላት በመንፈስ ቅዱስ ነውና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን። 1ኛ ቆሮ 2፤16 ይላል እግዚአብሔር እውቀትን ገልጦላቸዋልና። ሰዎች በተፈጥሯቸው ማወቅ የማይችሉትን ቅዱሳን እግዚአብሄር በሰጣቸው ስልጣን መሰረት ሲያውቁ እንመለከታለን።
5. ኢየሱስ ክርስቶሰ ፈራጂ ነው ቅዱሳንም እርሱ በሰጣቸው ስልጣን ይፈርዳሉ
ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉስ አምላክ ጌታ ስለሆነ ፈራጂ ነው። በሐጥአን የሚፈርድባቸው ለጻድቃን የሚፈርድላቸው ፍርድን የሚሰጥ እርሱ ኢየሱስ ነው። 2ኛ ጢሞ 4፡ 1 በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤ በህያዋንና በሙታን ላይ የሚፈርደው እርሱ ክርስቶስ ነው። ፍርድን የሚሰጥ እርሱ እግዚአብሔር የሆነ ክርስቶስ ነው። ከእርሱ ፍርድ ይወጣል እንጂ ልመና አይወጣም።

2ኛጢሞ 4፤ 8 ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ ጻድቅና ፈራጂ ነው። ፍርዱም በአንድና በሁለት ሰው የሚወሰን አይደለም በሁሉም ላይ የሚፈርደው እርሱ ነው። ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ያለው። መገለጡን ለሚወዱ ሁሉ ይፈርድላቸዋልና።

2ኛ ቆሮ 5፡ 10 መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፥ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና። መፅሐፍ ቅዱስ ፍርድ እንዳለ ይነግረናል። ይህን ፍርድ ደግሞ በእያንዳንዳችን ላይ የሚደረግ ነው። በእያንዳንዳችን የሚፈረደውን ፍርድ የሚፈርደው እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ታዲያ ኢየሱስ ሲፈርድ መጀመሪያ ለምኖ ይሆን የሚፈርደው ? አይደለም ኢየሱስ የሚፈርደው በስራችን መጠን ነው። እርሱ እኛነታችንን ያውቃል በስራችን መጠንም ይፈርዳል።

ራዕ 22፤ 12፡ እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ :: ክርስቶስ ስራችንን ስለሚያውቅ እንደስራችን መጠን እንደ ሃይማኖታችን መጠን ፍርድን ይሰጣል። ፍርድን ሲሰጥ ሰዎች አማልደን ይሉት ይሆንን ? አይባልም እርሱ ፈራጅ እንጂ አማላጂ አይደለምና። እንዲያውም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው ፍርድን የሚያደርገው እርሱ ኢየሱስ እንጂ አብ አይደለም። ይህ ሲባል የአብና የወልድ ፈቃድ የተበለያየ ነው ማለት አይደለም የአብም ሆነ የወልድ ፈቃድ አንድ ነው ሆኖም ፍርዱን የሚሰጠው የሚፈርደው እርሱ ኢየሱስ ነው። አብ በማንም አይፈርድም ፍርድ የእርሱ የወልድ ስልጣን ነው። ዮሐ 5-22-23 ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም :: ፈራጂ ወልድ ከሆነ እንግዲህ ወልድ የሌለው ስልጣን አለ ልንል እንችላለን ? የለም ወልድ ራሱ ነው የሚፈርደው የሚጸድቁትንም ሆነ ወደ ኮነኔ የሚሄዱትን የሚለይ የሚፈርድ እንደ ስራቸው የሚያስረክብ እርሱ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ጌታችን በሰማይና በምድር ፈራጂ እንደሆነ ሁሉ ቅዱሳንንም ይፈርዱ ዘንድ ስለጣንን ሰጥቷቸዋል። ቅዱሳንን ይፈርዱ ዘንድ ስልጣንን የሰጣቸው እራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማቴ 19፤28 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ። ቅዱሳን ማማለድ አይደለም እንዲፈርዱ እርሱ እግዚአብሔር ሾሟቸዋል ታዲያ እግዚአብሔርን ተሳስተሃል ብሎ ማን ይቃወመዋል እርሱ የወደደውን መስራት ይችላልና። እርሱ ካከበራቸውስ ማን ሊቃወማቸው ይችላል።
የተወደዳችሁ አንባቢያን ሆይ ቅዱሳን ኢየሱስ ክርስቶስን የመሰሉት እንዲሁ አይደለም። እነርሱ በህይወታቸው እግዚአብሔርን ስላስቀደሙ ከዚህ ዓለም ተድላና ደስታ ይልቅ እርሱን ስለወደዱ ቃሉን እለት እለት እያስታወሱ በህጉ ስለተጓዙ ነው። እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስን በመልካም ስራው በመከተል እርሱ እንደ ጾመ ስለጾሙ እርሱ እንደጸለየ ስለጸለዩ እርሱ የሚጠሉትን እንደወደደ ጠላቶቻቸውን ስለወደዱ እርሱ ድሆችንና ችግረኞችን እንዳከበረ የሰውን ልጂ ሁሉ ስላከበሩ እርሱ ደግሞ ክብራቸውን አበዛ በጸጋ ላይ ጸጋ ሰጣቸው። እንደዚያ ባይሆን ኖሮማ ቅዱሳን እንደእኛ ሰዎች ነበሩ ነገር ግን እንደእኛ ሰው ሲሆኑ በእምነታቸው ምክነያት ሰው የማይሰራውን ስራ ሰሩ። እኛም ሐዋርያው እንደተናገረ ቅዱሳንን ለመምሰል እንትጋ። ፍቅርንና ትህትናን እንላበስ ወንድሞቻችንን እንወደድ የተቸገሩትን እንርዳ የእግዚአብሔርን ቃል እንማር ቃሉንም ለማያውቁና ለማያምኑ እናስተምር ያን ጊዜ ቅዱሳንን እንመስላለን።ያን ጊዜ እግዚአብሔር ይባርከናል ያከብረናልም።
ቃሉን አውቀን በህይወታችን ተርጉመን እንድንጠቀም የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጂነት አይለየን!!!

ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን sex abuse ምን እንማራለን?

March 21, 2010

ሰሞኑን የዜና ማሰራጫዎች የካቶሊክ ቀሳውስት ያደረጉትን የህጻናት መድፈር በማረጋገጥ ቤተ ክርስቲያኗ በአደባባይ ይቅርታ እንድትጠይቅ አድርገዋል። ይህ በትክክል ለማነኛቸውም አካል ውርደት ነው። ለቤተ ክርስቲያኗ ፤ ለቀሳውስቱ ፤ ለተደፋሪዎች ህጻናት ፤ለቤተሰቦቻቸውና በካቶሊክ ውስጥ ድርሻ ያላቸው ሰዎች ሁሉ ያፈሩበት ነው። ሆኖም ዘገባዎች እንዳመለከቱት ይህ አይነት ድርጊት አሁን ቢባባስም የቆየ እንደነበረ አንዳንዶች ይናገራሉ። ታዲያ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ቅድመ ክትትል ባለማደረጓና በጊዜው እርምት ባለመውሰዷ ከ500 የሚበልጡ የህጻናትን መድፈር የክስ ኬዞች ተመዝግበው ይገኛሉ። http://news.bbc.co.uk/2/hi/europe/8577740.stm

በእኛ ቤተ ክርስቲያንም ምንም አንኳን አብዛኛዎቹ አባቶቻችን ጨዋዎችና እግዚአብሔርን በፍጹም ልባቸው ከማገልገል ውጭ ሌላ የማያውቁ ቢሆንም አንዳንዶች በተለይም ደግሞ ራሳቸውን ባህታውያን ብለው ከሚጠሩት ወገኖች የሚያታልሉ እንዳሉ አንዳንድ ሰዎች ይናገራሉ። እኔ በአይኔ ባላየውም አንድ ባህታዊ የዛሬ አንድ አመት አካባቢ አስገድዶ በመድፈርና በግድያ ክስ ተከሶ እንደተያዘ ሰምቻለሁ። ታዲያ ምዕመናኑ እንዲህ አይነት ሰዎችን በተለይም ቄስ ሳይሆኑ ቄስ ነኝ ባህታዊ ሳይሆኑ ባህታዊ ነኝ የሚሉና በክርስቶስ መንፈስ ሳይሆን በስጋ መንፈስ የሚመሩ ሰዎችን ሊያውቅባቸውና ሊያጋልጣቸው ይገባል። ሐሰተኞችን ካላጋለጥንና ቻሌንጅ ካላደረግን ከጊዜ በሗላ እውነተኞችንም እንደ ሐሰተኞች ቆጥረን እንድንጠላ ያደርገናል። ማነኛውንም አይነት አቢዩዝ ሰምቶ ዝም ከማለት ማጣራቱና ለሚመለከተው ክፍል ማሳወቁ ለቤተ ክርስቲያኗም ይሁን ለሰውየው ጠቀሜታው የጎላ ነው ብየ አምናለሁ።

Please forward your ideas on the issue.

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው ? ክፍል አምስት

March 15, 2010

የኢየሱስ ክርስቶስ ስልጣን፡

መጽሐፍ ቅዱስ ስለኢየሱስ ነግሮ እንዲሁ አልተወንም። ይልቁንም ስልጣኑን ጭምር አስረግጦ ይናገራል እንጂ። ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ስለሆነ አምላክ ስለሆነ ጌታ ስለሆነ ፈጣሪ ስለሆነ የአምላክ ስልጣን ሁሉ ለእርሱ አለው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ስልጣን እንዳለው ተመራምረን እንድንደርስበት ብቻ አልተወንም በሚገባ ልናውቃቸው የሚገቡ የኢየሱስ ስልጣኖችን ጠቅሶልናል።

በመሆኑም ካለው አምላካዊ ስልጣን ውስጥ በቀላሉ የምንረዳቸውን የተወሰኑትን እንጠቅሳለን።
1.ኢየሱስ ክርስቶስ ፈራጂ ነው፦ ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉስ አምላክ ጌታ ስለሆነ ፈራጂ ነው። በሐጥአን የሚፈርድባቸው ለጻድቃን የሚፈርድላቸው ፍርድን የሚሰጥ እርሱ ኢየሱስ ነው።
2ኛ ጢሞ 4፡ 1 በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤ በህያዋንና በሙታን ላይ የሚፈርደው እርሱ ክርስቶስ ነው። ፍርድን የሚሰጥ እርሱ እግዚአብሔር የሆነ ክርስቶስ ነው። ከእርሱ ፍርድ ይወጣል እንጂ ልመና አይወጣም።

2ኛጢሞ 4፤ 8  ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ ጻድቅና ፈራጂ ነው። ፍርዱም በአንድና በሁለት ሰው የሚወሰን አይደለም በሁሉም ላይ የሚፈርደው እርሱ ነው። ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ያለው። መገለጡን ለሚወዱ ሁሉ ይፈርድላቸዋልና።

2ኛ ቆሮ 5፡ 10 መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፥ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና። መፅሐፍ ቅዱስ ፍርድ እንዳለ ይነግረናል። ይህን ፍርድ ደግሞ በእያንዳንዳችን ላይ የሚደረግ ነው። በእያንዳንዳችን የሚፈረደውን ፍርድ የሚፈርደው እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ታዲያ ኢየሱስ ሲፈርድ መጀመሪያ ለምኖ ይሆን የሚፈርደው ? አይደለም ኢየሱስ የሚፈርደው በስራችን መጠን ነው። እርሱ እኛነታችንን ያውቃል በስራችን መጠንም ይፈርዳል።

ራዕ 22፤ 12፡ እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ :: ክርስቶስ ስራችንን ስለሚያውቅ እንደስራችን መጠን እንደ ሃይማኖታችን መጠን ፍርድን ይሰጣል። ፍርድን ሲሰጥ ሰዎች አማልደን ይሉት ይሆንን ? አይባልም እርሱ ፈራጅ እንጂ አማላጂ አይደለምና።
እንዲያውም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው ፍርድን የሚያደርገው እርሱ ኢየሱስ እንጂ አብ አይደለም። ይህ ሲባል የአብና የወልድ ፈቃድ የተበለያየ ነው ማለት አይደለም የአብም ሆነ የወልድ ፈቃድ አንድ ነው ሆኖም ፍርዱን የሚሰጠው የሚፈርደው እርሱ ኢየሱስ ነው። አብ በማንም አይፈርድም ፍርድ የእርሱ የወልድ ስልጣን ነው።
ዮሐ 5-22-23 ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም :: ፈራጂ ወልድ ከሆነ እንግዲህ ወልድ የሌለው ስልጣን አለ ልንል እንችላለን ? የለም ወልድ ራሱ ነው የሚፈርደው የሚጸድቁትንም ሆነ ወደ ኮነኔ የሚሄዱትን የሚለይ የሚፈርድ እንደ ስራቸው የሚያስረክብ እርሱ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

2. ኢየሱስ ይራራል ይቅር ይላል ይምራል፦
ኢየሱስ ክርስቶስ ስልጣኑ መፍረድ ብቻ አይደለም። ምህረት የሚገባቸውን ወደ እርሱ የሚቀርቡትን ይቅር ማለት የሚችል የሚምር ነው።
ኢየሱስ ይራራል፡ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ ፈራጂ ስለሆነ የሚያዝንላቸውንና ወደ እርሱ ለመመለስ ፍላጎት ያላቸውን ሊራራላቸው ይችላል። እግዚአብሔር ሩህሩህ ስለሆነ ኢየሱስም እግዚአብሔር ስለሆነ ሩህሩህ ነው። ስለዚህ ይራራል ይምራል ይቅር ይላል።
ዕብ 4፤ 15 ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። የኢየሱስ በእግዚአብሔርነቱ ሩህሩህ ከመሆኑም በተጨማሪ የዚህ አለምን ፈተና እንደኛ ሰው ሆኖ ያየ ነው። በመሆኑም እርሱ ይራራል።

ኢየሱስ መማር ይችላል (ይምራል )፡ እግዚአብሔር መሐሪ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስም እግዚአብሔር ስለሆነ ይምራል። መማር ይችላል። መቅጣት መፍረድ እንደሚችለው ሁሉ መማርም ይችላል።
ዕብ 2፡ 17 ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው :: ኢየሱስ በራሱ ምህረት መስጠት የሚችል ነው። ምህረት ለመስጠት ሌላ አካልን መጠየቅ አያስፈልገውም ራሱ መማር ይችላል እርሱ እግዚአብሔር ነውና።

ኢየሱስ ሀጢያትን ይቅር ይላል፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ሐጢያትን በራሱ ይቅር ማለት መማር የሚችል ነው። እንደ ቅዱሳን በእግዚአብሔር ስም ወይም በሌላ በሁለተኛ ወገን ሃይል አይደለም የሚያደርገው በራሱ ይቅር ማለት ማስተስረይ የሚችል ነው። ቅዱሳን ሰዎች በእግዚአብሔር ስም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ብለው ሐጢያትን ሊያስወግዱ ይችለሉ። እግዚአብሔር ይፍታህ እግዚአብሔር ይፍታሽ እንዲሉ። በሽተኞችንም ቅዱሳን ሲፈውሱ በእግዚአብሔር ስም ተፈወሰ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሳና ተመላለስ ይላሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሐጢያትን የሚያስወግደው ወይም ይቅር የሚለው በሽተኞችንም የሚያድነው የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ አይደለም። በራሱ ስልጣን ይቅር ማለት ማዳን የሚችል ነው። ራሱ ባለቤት ስለሆነ።
ዮሐ 5፡ 8 ኢየሱስ። ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው። እንዲሁም በሌላ ቦታ ኢየሱስ አንተ ልጂ ሐጢያትህ ተሰረየችልህ ሲል እናየዋለን። ኢየሱሰ ክርስቶስ በራሱ ሐጢያትን ማስተስረይ ስልጣን አለውና።

ማጠቃለያ፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ስልጣኑ የአምላክ ስልጣን ነው። ይህችን ዓለም የሚያሳልፍ ኢየሱስ ነው። ፍርድን የሚሰጥ እርሱ ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ እንደሚፈርድ ሁሉ ይራራል ይምራል ይቅር ይላል። በክርስቶስ ላይ የሚነሱ አንዳንድ አለመረዳቶችን ወደፊት እናነሳለን። በመጀመሪያ ግን ስለእርሱ ማንነት እንናገር።

ምስጋናና አምልኮ ለተሰቀለው ለድንግል ማርያም ልጂ ለኢየሱስ ክርስቶስ ይሁን። አሜን

ለታምራቱ መታሰቢያን አደረገ፡ ደብረ ዘይት

March 7, 2010

የክርስትና ጥቅሙና አላማው አንድና አንድ ነው። እርሱም የክርስቶስን መንግስት መውረስ ነው። ምን አልባት ሰዎች በትክክለኛው የክርስትና ህግ ከሄዱ ከሐጢያት በመቆጠባቸው በስጋዊ ህይወታቸው ከሌሎች በተሻለ መልኩ ጤነኞችና ደስተኞች ይሆኑ ይሆናል። እግዚአብሔርም በዚህ ምድር ህይወታቸውን ሊባርክላቸው ይችላል። ሆኖም የክርስትና ዋናው ቁም ነገር በዚህ ምድር ተደስቶ መኖር ብቻ አይደለም። ጌታችን ሰው አለምን ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎል ምን ይጠቅመዋል እንዳለ/ማቴ 16፤26/ የክርስትና ትርፉ የነፍንስን ደስታ ማትረፍ ነው።
ደብረ ዘይት ማለት የዘይት ተራራ ማለት ነው። ይህም ማለት የዘይት ዛፎች ያሉበት ተራራን ለመግለጽ ነው። እንደ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን እምነትና ስርዓት የጌታ መምጫ በሰው ህሌና በእያንዳንዱ ሰው ሁል ጊዜ ሊኖር እንደሚገባው ቢታወቅም የክርስቶስን ዳግም መምጣት አስረግጣና አስፋፍታ የምትናገርበት ቀናት አላት። ከእነዚህም ቀናት ውስጥ አንዱ ዛሬ የምናከብረው የደብረ ዘይት በዓል ነው።

በአሉ በቦታ ስም ቢጠራም የሚያመለክተው ግን የክርስቶስን ዳግም መምጣት ትምህርት የተሰጠበትን ቦታ ነው። የሚታሰበው ትምህርቱና ወደፊት ክርስቶስ መምጣቱ እንጂ ቦታው አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት እያየት እንደሄደ ሁሉ ተመልሶ ይመጣል።ይመጣል አይቀርም የወጉትም ሁሉ ፊቱን ያዩታል ያውቁታል። ማን እንደነበረ ይረዳሉ የሰቀሉት የገደሉት ያላገጡበት የተፉበት ያልተቀበሉት ያሳደዱት እርሱ እግዚአብሔር እንደሆነ ያውቃሉ። እርሱ ለጻድቃን ሊፈርድላቸው ለሐጢያተኞች ሊፈርድባቸው ይመጣል።
ክርስቶስ ይመጣል ምድርን ያናውጣል
ክርስቶስ ይመጣል አለምን ያቀልጣል
ክርስቶስ ይመልጣል ክፉዎችን ይቀጣል
ክርስቶስ ይመጣል ለጻድቃን ዘለዓለማዊ ደስታን ይሰጣል።
የክርስቶስ ዳግም መምጣት በክርስቶስ እንደተነገረ መላዕክትም ለሐዋርያት መስክረዋል። ከዚያም አስቀድመው አባቶች ነቢያት እግዚአብሔር እንደሚመጣ ተናግረዋል።/ሐዋ 1፤11/
ለዚህ ነው ቅዱስ ዳዊት፡ መዝ 50፡3-5 ከክብሩ ውበት ከጽዮን እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል። አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፤ እሳት በፊት ይቃጠላል፥ በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ። ኢየሱስ ክርስቶስ
ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረዘይት ያስተማረው ስለዳግመኛ መምጣቱና ስለምጻቱ ምልክነት ነው። በምጻቱ ጊዜ ስለሚፈጸሙ ነገሮች፤ በምጻቱ ጊዜ ሊደረግ ስለሚገባ ጥንቃቄና በምጻቱ ለመጠቀም መሆን የሚገባንን ነገር አስረድቶናል። ቃሉ በሙሉ በማቴ 24 ያለ ሲሆን አለፍ አለፍ ብለን እንመልከት።

1. የምጻቱ ዋዜማ /ምልክት/
ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጥ ካስተማራቸው ትምህርቶች ውስጥ አንዱ ስለመምጣቱ ነው። በመጀመሪያ አለሙም ሆነ መላዋ ነገር ሐላፊ መሆኗን ካስረዳ በሗላ የዘረዘረው ምልክቱን ነበር።
– ብዙዎች። እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ።
– ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው።
– ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤
– እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።
– በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።
– በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤
– ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤
– ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች።
እዚህ ላይ ያነሳቸው ሁለቱ ዋና ዋና ነጥቦች በክርስቶስ ስም በክርስትና ስም ብዙ ሐሰተኞች የሚመጡ መሆናቸውና በአለም ላይ ጭንቅ፤ ጥል፤መከራ መምጣት ነው።ሆኖም እነዚህ ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያዎች ናቸው አለእንጂ መጨረሻዎች አይደሉም። እንደ እውነቱ ከሆነ የተዘረዘሩት ምልክቶች በአጠቃላይ እየተፈጸሙ ያሉ ስለመሆናቸው የምናውቀው ጉዳይ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝ ከሚሉት አንስቶ ሐሰተኞች ነቢያት የመጡበት ግልጥ ጊዜ ነው። ዛሬ ኢየሱስ ይመጣል ብለው የሚሰብኩ ሐሰተኞች ነቢያት ራሱ አሉ።

ከላይ የተጠቀሱት ህዝብ በህዝብ ላይ መንግኢት በመንግስት ላይ መነሳቱ የምድር መናወጡ ከመቸውም ጊዜ በላይ በዘመናችን እየተፈጸመ ስለመሆኑ መረጃው በእጃችን ነው። በወንድማማች መካክል ፍቅር ስለመጥፋቱ አንዱ አንዱን አሳልፎ ስለመስጠቱ ስለመካሰሱም ሌላ ቦታ መሄድ ሳያስፈልገን በዙሪያችን ያሉትን ሁኔታዎች ማየት በቂ ነው። ታዲያ ይህንን ስናይ የክርስቶስ መምጣት የተቃረበ ስለመሆኑ ጥርጥር የለም።

ታዲያ ኢየሱስ የሚመጣ ከሆነ ምን እናድርግ። ክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣት ሁል ጊዜ የሚጠባበቅ ነው። በህይወቱ ሁልጊዜ ዝግጁ ሆኖ የሚኖር ነው እንጂ ዛሬ ይመጣ ይሆንን ብሎ የሚደነብር የሚረበሽ ሊሆን አይገባውም። ሁሌ መዘጋጀት ግን ያስፈለጋል። አንዳንዶች ኢየሱስ ነገ ወይም የዛሬ አመት ይመጣል ብለው እንደሚያውጂት ግን የክርስቶስን መምጫ መናገር አንችልም። ይህ የመምጫው ምልክት የሆነው ጊዜ ለምን ያክል እንደሚቆይ አናውቀም። ገና ብዙ ሊቆይ ይችል ይሆናል ሊያጥርም ይችላል። ስለቀኑና ሰዓቱ አናውቅም። ወልድ እንኳን ለእኛ ለመረጣቸውና ለሾማቸው ለሐዋርያቱ እንኳን አልነገራቸውም። እንዲያውም በአብ ልብነት ተቀምጣ ትኖራች እንጂ አትነገርም ሲል ከአብ ውጭ ማንም አያውቃትም ብሎናል።

2. ማስጠንቀቂያው፡
ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚመጣ ብቻና በዚያ ዘመን ምን እንደሚሆን ተናግሮ አልቀረም። ከምን ልንጠበቅ እንደሚገባም ከማስጠንቀቂያ ጋር ተናግሯል። ያስጠነቀቀው አደጋ ስላለ ነው። ቃሉን አልፈን ብን ሄድ አደጋ ስለሚገጥም ከዚህ አደጋ እንድንድን ማስጠንቀቂያውን አስረግጦ ነግሮናል። የተናገራቸው ማስጠንቀቂያዎች በዝርዝር ሲቀመጡ፡
– ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ።
– በዚያን ጊዜ ማንም። እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም። ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤
– እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ።
የክርስቶስ ማስጠንቀቂያዎች የተሰጡት ከላይ የሚመጡ ችግሮችን በእርሱ የሚያስመሰሉትን ነገር ግን በትክክል እርሱን ሊያከብሩና ሊያመልኩ የማይወዱትን እንዳንከተል ነው። በትክክል ኢየሱስ እንደተናገረው የሚመጡት ሐሰተኛ ነቢያት እርሱን የሚመስሉ በእርሱ ስም የሚመስሉ ነገር ግን በውስጣቸው ሞትን የያዙ ናቸው።

ሐሰተኛ ነቢያቱ ድንቅ ድንቅ ታምራት ከማድረጋቸው የክርስቶስ ሐዋርያ ነን ከማለታቸው የተነሳ ብዙዎችን ያስታሉ ያታልላሉ።ማቴ 24፤24 ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ። የተመረጡትን በወንጌል አገለግጎት ያሉትን ባህታዊያንን መነኮሳቱን ህይወታቸውን ለእግዚአብሔር ብቻ የሰጡትን እንኳን ሳይቀር ያስታሉ። ለዚህ ነው ማስተዋል የሚያስፈልገው። መንፈስን ሁሉ አትቀበሉ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር እንደሆኑ ፈትኑ እንደተባለ ዛሬ ያልን መንፈስ ሁሉ ልንመረምር ግድ ነው።

3. ሊኖረን ስለሚገባው ውሳኔ፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ምን እንደሚሆን ተናግሮና አስጠንቅቆ ብቻ አላቆመም። ወደ ፊት በህይወታችን ልናደርገው ስለሚገባን ነገርም አስረግጦ ነግሮናል። ልናደርገው ከሚገባን ነገሮች ውስጥ ለመጥቀስ ያክል
– እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።
– በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥
– በሰገነትም ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፥
– በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ።
በነዚህ መልእክቶቹ ለማስተላለፍ የፈለገው ባላችሁበትና በተረዳችሁነት ነገር ጸንታችሁ ቁሙ አትናወጡ ነው። ይህን ሲል ግን ታዲያ በእውነት ላይ ያላችሁ ባላችሁበት ጽኑ ማለቱ እንጂ በሐሰት መንገድ ያላችሁ በአመጻችሁ ጽኑ አለማለቱን ልንገነዘብ ይገባል።
– ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፤ መስራት በማትችሉበት ሰዓት እንዳይሆን ተዘጋጅታችሁ እንድትጠብቁ ጸልዩ ሲለን ነው።
– ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። ሁላችን ነቅተን እንድንጠብቅ እንዳናንቀላፋ ነው። የእርሱን መምጫ ስለማናውቅ ጊዜው የዘገየ መስሎን እንዳንቀር ሲያስተምረን ነው።
ለፍርድ የሚመጣው መፍረድ የሚችለው አምላክ ኢየሱስ ነው። የሚመጣው አማላጂ አይደለም። የሚመጣው ነቢይ አይደለም። የሚመጣው ሰው አይደለም። የሚመጣው እውነተኛው አምላክ መፍረድ የሚችል አልፋና ኦሜጋ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ለታምራቱ መታሰቢያን አደረገ
ወስበሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል።

ጌታ ሆይ በፍርድ ሰዓት በቀኝህ ከሚቆሙት እንድንሆን አንተ አርዳን። አሜን።