ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው? ክፍል ሰባት

ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዲሲ ኪዳን ሊቀ ካህን ነው፦

ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዲስ ኪዳን ሊቀ ካህን /ካህናት አለቃ / ነው። የተለዩ የእግዚአብሔር ካህናት ስላሉ የእነርሱ አለቃ መሆኑን ሲያመለክት ክርስቶስን ሊቀ ካህናት ይለዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህንነት እንዴት ነው ? የኢየሱስ ሊቀ ካህንነት እንደ ኦሪት ሊቃነ ካህናት ነውን ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለኢየሱስ ሊቀ ካህንነት ምን ይላል የሚለውን እንመለከታለን።
መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስን ሊቀ ካህነነት ከሌዋዊያን ሊቃነ ካህናትና ከሰላም ንጉስ ከመልከ ጼዴቅ ሊቀ ካህንነት ጋር አነጻጽሮ ይነግረናል።

የመልከ ጼዴቅና የኢየሱስ ክርስቶስ ካህንነት
-መልከ ጼዴቅ ፍጹም ጻድቅ የነበረ፤ ጻድቁ አብርሃም ከእርሱ የተባረከለት ካህን ነበር።ዕብ 7፤ 1-3፣ ዘፍ 14፤ 17-20 ኢየሱስ ክርስቶስም ፍጹም ጻድቅ ሁሉን የባረከ የሚባርክ ነው።
-መልከ ጸዴቅ ሹመቱ ለዘለዓለም ነው፤ የአይሁድ ሊቃነ ካህናት ሹመት የሚያልፍ የሚተካ ነበር ለምሳሌ ዘሁ 20፤ 22 ላይ እንደምናገኘው የአሮን ሊቀ ካህንነት ለልጁ ለአላዛር ሲሰጥ እናገኛለን። የመልከ ጸዴቅ ሊቀ ካህንነት ግን ለዘለዓለም ነበር። የኢየሱስ ክርስቶስም ሊቀ ካህንነት ለዘለዓለም ያለ የሚኖር ነው በዚህ ጊዜ ያልፋል አይባልም። ዕበ 7፤ 1-3፤መዝ 109፤ 4 ፡ ዕብ 5፤ 6
-መልከ ጸዴቅ ሹመቱን ከማንም አላገኘውም። ሌሎች ሊቃነ ካህናት በሰው ይሾሙ ነበር። መልከ ጸዴቅ ግን ሹመቱን ከእግዚአብሔር አግኝቶታል እንጂ ማንም አልሾመውም። ኢየሱስ ክርስቶስም ሹመቱ ከሰማይ ከአባቱ ዘንድ የሆነች ናት እንጂ ሰው ሾመው አይባልም።
-መልከ ጸዴቅ ያቀረበው መስዋዕት ህብስትና ጽዋ ነበር ዘፍ 14፤ 17-20 ኢየሱስ ክርስቶስም ለሐዲስ ኪዳን መስዋዕት ይሆነን ዘንድ ሰርቶ ያሳየን ስጋውንና ደሙን ነው።ማቴ 26፤ 57-65

መልከ ጸዴቅ የክርስቶስ ምሳሌ ነው። በመሆኑም መልከ ጸዴቅን ከክርስቶስ ጋር አነጻጽሮ ሐዋርያው ብዙ ተናግሯል። በአንጻሩ የአይሁድ ሊቃነ ካህናት ድካም ያለባቸው በመሆናቸው በአሉታዊ ጎኑ ከክርስቶስ ሊቀ ካህንነት ጋር አነጻጽሮ እንደሚከተለው ያቀርባቸዋል።

የኦሪት /የአይሁድ ሊቃነ ካህናት እና የኢየሱስ ሊቀ ካህንነት፡

የኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህንነት ዘለዓለማዊ ነው ነገር ግን አንድ ጊዜ ራሱን መስዋዕት አድርጎ ባቀረበ ጊዜ የተፈጸመ ነው። መስዋዕቱ ዛሬ ያው ነው ለሚያምኑበት ሁሉ ያለ የማያልፍ ነው ሐዋርያው የኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህንነት ከአይሁድ ሊቀ ካህንነት የተለየ እንደሆነ ሲናገር ዕብ 7፤ 27 እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።

-የኦሪት ሊቃነ ካህናት ያቀርቡ የነበረው የእንስሳትን ደም ነበር ኢየሱስ ግን ያቀረበው የራሱን ደም ነው

የኦሪት ሊቃነ ካህናት ወደ እግዚአብሔር እየለመኑ ሐጢያትን ያስተሰርዩ ነበር። በተለይም በአመት አንድ ጊዜ ካህኑ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ደም ይዞ በመግባት ስለህዝቡና ስለራሱ ጸሎት ያቀርባል። ዘጸ 30፤ 10 ይህንን አንዱ ሊቀ ካህን ሲሞት በሌላው እየተካ መስዋዕትን ያቀርባል። ዕብ 9፡ 7 በሁለተኛይቱ ግን ሊቀ ካህናት ብቻውን በዓመት አንድ ጊዜ ይገባባታል፥ እርሱም ሰለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ስሕተት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ አይገባም፤
ለዚህ ነው ሐዋርያው ዕብ 9፤ 25 12 የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም። ያለው።በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎች ወይም በጥጆች ደም አይደለም። የሌላውን ደም ሳይሆን የራሱን ደም ነው ያቀረበው። በእንስሳት ደም አይደለም ዓለም የዳነው በእርሱ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም እንጂ።

-የኦሪት ሊቃነ ካህናት በልመናና በእንስሳት ደም ሐጢያትን ያስተሰርዩ ነበር ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ በደሙ በራሱ ነው ሐጢያትን ያስተሰረየው
ዕብ 1፤ 33 እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤

-የኦሪት ሊቃነ ካህናት ሞትና እርጂና ነበረባቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ለሊቀ ካህንነቱ ሽረት /መለወጥ / የለበትም
የኦሪት ሊቃነ ካህናት ድካም ነበረባቸው ሐጢያት ይሰራሉ በሌላ በኩል ሰዎች ስለሆኑ ለዘለዓለም መኖር አይችሉም። ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እርሱ ከሐጢያት የራቀ ፍጹም ነው እርሱም ለዘለዓለም የሚኖር የማያልፍ ነው። ዕብ 7፡ 28 ሕጉ ድካም ያላቸውን ሰዎች ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣ የመሐላው ቃል ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ይሾማል።

-የኦሪት ሊቃነ ካህናት በእየጊዜው እግዚአብሔር ይቅር እንዲል መለመን ነበረባቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አንድ ጊዜ ባደረገው የመስቀል ስራ /ሊቀ ካህንነት / አዳነን
ዕብ 9፤ 26-27 ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ያደረገው የማዳን ስራ እስከዘለዓለም በስሙ ለሚያምኑ ሁሉ የተከፈለ ዋጋ ነው። ዛሬ በቤተ የሚሰዋው መስዋዕት በእለተ አርብ ከፈሰሰው ደሙና ከተቆረሰው ስጋው ጋር አንድ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክነቱ ፤ በሊቀ ካህንነቱ ዛሬም ከሞተ ስራችን ነጻ ያደርገናል። ደሙ ከሐጢያት ሁሉ የነጻልና። 1ኛ ዮሐ 2፤ 1 ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።

One Response to “ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው? ክፍል ሰባት”

  1. petros (Peter) Says:

    እግዚአብሔር ይባርክህ

Leave a comment