ቅዱሳን እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ

በዚህ ርዕስ የቅዱሳንን ማንነትና ክርስቶስ እርሱን እንዲመስሉ የሰጣቸውን ስልጣን እንመለከታለን። እግዚአብሔር ለስጦታው ወደር ለቸርነቱም ቁጥር የለውምና በእርሱ የሚያምኑ እርሱን እንመስሉ ስለጣን ሰጥቷል። ይልቁን በስጋ የተገለጠው አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ  እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፥ /ዮሐ 14፤12/ ብሎ እንዳስተማረ በክርስቶስ እስከሞት ድረስ ያመኑ ቅዱሳን እርሱን እንዲመስሉ አድርጓል። በመሆኑም ከዚህ ቀጥለን የቅዱሳንን ማንነትና በምን ክርስቶስን እንደሚመስሉ በተወሰነ ደረጃ እንመለከታለን።
ኢየሱስ ክርስቶስ የአማልክት አምላክ የጌቶች ጌታ የነገስታትም ንጉስ ነው።/ሮሜ 9፤5 ፤1ኛ ዮሐ 5፤19 ራዕ 17፤14 / ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለማትን የፈጠረ እግዚአብሔር ነው።/ዮሐ 1፤1 ቆላ 1፤ 16-17/ እርሱ ፈጣሪ ቢሆንም አዳም በበደለው በደል ምክነያት ሞት ስለተፈረደበት አዳምን ከሞት ነጻ ለማድረግ ከሰማያት ወርዶ ክድንግል ተወልዶ እንደ እኛ ሰው ሆኖ በመካከላችን ተመላልሶ አርአያውን ትቶልን ሄዷል። በዚህም ከእርሱ እንድንማር አስረድቶናል። ከእኔም ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝና። ማቴ 11፡ 39 እንዲሁም ቅዱስ ጴጥሮስ ክርስቶስ ደግሞ እርሱን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለእናንተ መከራን ተቀብሏልና። 1ኛ ጴጥ 2፤ 21 ይላል በዚህም ኢየሱስ ክርስቶስን እንደምሳሌ አድርገን እርሱን እንድንመስል ለማስረዳት ነው። ማነኛውም ክርስቲያን እርሱን ሊከተል እንደሚገባውና ከእርሱ ህይወት መማር እንደሚገባን ቤተ ክርስቲያን ታስተምረናለች።ቅዱስ ጳውሎስም እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተም እኔን ምሰሉ ይላል።
ቅዱሳን ኢየሱስን እንዲመስሉ እግዚአብሔር መወሰኑን ሲያስረዳ ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው።ሮሜ 8፤28-30 በዚህ ጥቅስ ላይ ቅዱሳንን አስቀድሞ እግዚአብሔር እንደጠራቸው የእግዚአብሔርልን ልጂ ኢየሱስ ክርስቶስን ይመስሉ ዘንድ እንደወሰነ ይናገራል። የልጁን መልክ ሲል እኛ የምናውቀውን ገጽ ማለት አይደለም የኢየሱስን ቅድስና ንጽሕና ክብር እንዲከተሉ ስራውን እንዲከተሉ እግዚአብሔር ወስኖላቸዋል። እንዲያውም እግዚአብሔር የልጁን መልክ የመሰሉ ቅዱሳንን ራሱ እንዳከበራቸው ሲገልጽ ያጸደቃቸውን ደግሞ አከበራቸው ይላል። ቅዱሳንን ያከበረ ራሱ እግዚአብሔር ነውና።
ቅዱሳን እንማን ናቸው?
ቅዱስ ማለትም የተለየ ማለት ሲሆን ቅዱሳን ሲሆን የተለዩ የሚለውን ያመለክታል። ቅዱሳን የተለዩ ናቸው ሲባልም ከዚህ አለም ርኩሰትና ሐጢያት የተለዩ ለእግዚአብሔር ክብር ራሳቸውን ያዘጋጁ ማለት ነው። ቅዱሳን ከራሳቸው ይልቅ ለእግዚአብሔር የኖሩ፤ አለምንና በእርሷ ያለውን የናቁ እነርሱም በአለም የተናቁ ፤ስለወገኖቻቸው በሐጢያት መውደቅ የሚያዝኑ ስለክርስቶስ መንግስት የመሰከሩ ናቸው።

ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳን ብላ የምትጠራቸው ቅዱሳን ሰዎች እግዚብሔርን በተለያየ መንገድ ሊያክብሩት ቢችሉም በአጠቃላይ ግን በሚከተሉት መልኩ ልንመድባቸው እንችላለን።

ቅዱሳን ሰማዕታት፡ ሰማዕት ማለት ምስክር ማለት ሲሆን ምስክርነታቸውን ለእግዚአብሔር ነው።እስከ ደም ጠብታ ድረስ ለእግዚአብሔር ሲሉ ራሳቸውን መስዋዕት ያደረጉና እውነትን የመሰከሩ ናቸው። የሰይፍ መሳል የእሳት መጋል አውነትን ከመመስከርና ስለእግዚአብሔር ሐያልነት ከመናገር ያላስቆማቸው ናቸው። ህይወታቸውን እስከመስጠትና እስከ መገደል ከቦታ ቦታ እስከመሰደድ ድረስ እግዚአብሔርን በህይወታቸው ያከበሩትን ቅዱሳንን ሰማዕታት እንላቸዋለን። እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የህይወትን አክሊክ አቀናጂሀለሁ ያለውን የክርስቶስን ቃል ይዘው የታመኑ ናቸው።/ ራዕ 2፤10/ ከነቢያት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ስለአንዲቱ እምነታቸው ስለእግዚአብሔር ክብር መከራ የሚቀበሉት ሁሉ ሰማዕታት እንላቸዋለን።

ቅዱሳን ጻድቃን፡ ጻድቃን ማለት እውነተኞች ማለት ነው። እነዚህም ሐዋርያው ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ። እንዳለው /ዕብ 11፤38/ ከዚህ ዓለም ራሳቸውን ለይተው በጾምና በጸሎት ራሳቸውን ጠምደው እግዚአብሔር ሲያገለግሉ የኖሩ አባቶችና እናቶች ጻድቃን ይባላሉ። እነደ አብርሃምና እንደ ኢዮብም በዓለም እየኖሩ እግዚአብሔርን በህይወታቸው ሙሉ ያከበሩ ቅዱሳንም ጻድቃን ይባላሉ።

ቅዱሳን ሊቃውንት፡ ቅዱሳን ሊቃውንት የምንላቸው በህይወታቸውና በኑሯቸው እየመሰከሩ የክርስቶስን የክብር ወንጌል ለዓለም ያስተዋወቁ ናቸው እኒሁም ከሐዋርያት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ የሚነሱ በእውነተኛው የክርስትና ትምህርት ላይ የታነጹ የሚያንጹም ናቸው። ተከራክረው መናፍቃንን የሚረቱ ከሐዲያንን የሚያሳምኑ ከእውቀታቸው ጋር ህይወታቸውን ለእግዚአብሔር ያስገዙትን ሊቃውንት እንላቸዋለን።
ታዲያ ቅዱሳን እንዴት ኢየሱስን ይመስሉታል?
ቅዱሳን እግዚአብሔር የሆነውን እርሱን ኢየሱስን ይመስላሉ ስንል ቅዱሳን አምላክ ናቸው ማለት አይደለም። ቅዱሳን እግዚአብሔር ራሱ ስላከበራቸው ከእግዚአብሔር የተነሳ የተከበሩ ናቸው። ስለጣናቸውን ክብራቸውን ጸጋቸውን ሁሉ ከእግዚአብሔር ያገኙት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን በራሱ በባህርይው የከበረ ነው። እርሱ ፈጣሪ ነው አርሱ አምላክም ነው እርሱ አክባሪ ነው የሚያከብረው አይፈልግም ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ሆኗልና።
ቅዱሳን እርሱ በሰጣቸው ጸጋ መሰረት ኢየሱስ ክርስቶስን ይመስላሉ። ታዲያ እንዴት ይመስሉታል ማለታችን አይቀርም። ጌታችን ሲያስተምር በዮሐ 8፤12 እኔ የአለም ብርሃን ነኝ ይላል እንዲሁም ማቴ 5፡14 ላይ ቅዱሳኑን እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። ይላቸዋል። እግዚአብሔር ቅዱሳንን እንዴት እንደሚያከበራቸውና ጸጋውን እንዴት እንዳበዛላቸው የሚያሳይ ነው። እርሱን ብርሃኑን ስለተከተሉ እነርሱ ደግሞ ለዓለም ብርሃን ናቸውና። በመሆኑም ከዚህ ቀጥለን ቅዱሳን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚመስሉበትን አንዳንድ ጉዳዮች እንመለከታለን።
1. ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝ ፈዋሽ ነው ቅዱሳንም የመፈወስ ጸጋ ሰጥቷቸዋል
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መድሓኒት ነው። እግዚአብሔር ፈዋሽ ስለሆነ የሚሳነውም ስለሌለ እርሱ ከማናቸውም ነገር ማዳን ይችላል። ስለኢየሱስ ክርስቶስ ፈዋሽነት መጽሐፍ ቅዱስ በጥልቀት ይናገራል። ከሞተ አራት ቀን የሆነውን አልአዛርን ከመቃብር አስነስቶታል (የሐ 11)፤ የሞተችዋን የኢያንሬዎስን ልጂ አስነስቷል፤ ሲወለድ ጀምሮ አይን ያልነበረውን ሰው አይን ሰርቶለታል /ዮሐ 9/፤ ሁለቱን እውሮችም አይናቸውን አብርቷል /ማቴ 9/ ። ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህም አልፎ ጨርቁ እንኳን ለሚያምኑበት ይፈውስ ነበር። አስራ ሁለት አመት ደም ይፈሳት የነበረችዋ በሽተኛ ሴት ልብሱን የነካሁ እንደሆነ እፈወሳለሁ ብላ በማመኗ ብቻ ልብሱን ነክታ ተፈውሳለችና።

ቅዱሳን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚከተሉ እግዚአብሔርን የሚያከብሩ ስለሆኑ ቅዱሳን የመፈወስ ስለጣንን ከኢየሱስ ክርስቶስ ተቀብለዋል። አስራ ሁለቱንም ጠርቶ በእርኩሳን አጋንንት ላይ ስልጣን ሰጣቸው እንዲል ። ሐዋርያትም ይሁኑ ነቢያት ከዚያም በሗላ የተነሱ ቅዱሳን አምላካቸውን ክርስቶስን ከመሰሉበት አንዱ ነገር በእርኩሳት መናፍስት ላይ ስልጣን ስላላቸው ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ ሀይልና ስልጣን አጋንንትን እንዳስወጣ ሁሉ ቅዱሳን ደግሞ የእርሱን ስም መከታ አድርገው በስላሴ ስም፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም፤ በእግዚአብሔር ስም ፤ በሐዋርያት ስልጣን አጋንንትን ያስወጣሉ። ለምሳሌ ያክል በሐዋ3፤2 ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ፥ ሰዎች ተሸክመው መልካም በሚሉአት በመቅደስ ደጅ በየቀኑ ያስቀምጡት የነበሩ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ አንካሳ የሆነ አንድ ሰው ነበረ። ይህንን ሰው ሐዋርያቱ ቅዱስ ጴጥሮስና ዮሐንስ ፈውሰውታል።ሐዋ 3፤8 ተመሳሳይ የፈውስ ታሪክ በሐዋ 9፤34 ላይም እናገኛለን ሽባውን ቅዱስ ጴጥሮስ ፈውሶታልና።
ቅዱሳን በመፈወስ ብቻ ሳይሆን ሙታንንም ያስነሳሉ፦ ቅዱስ ጴጥሮስ ከሞተች በሗላ ጣቢታን አስነስቷል /ሐዋ 9፤41/ ቅዱስ ጳውሎስም እንዲሁ ከፎቅ ላይ ወድቆ የሞተውን ክርስቲያን አድኖታል። ሐዋ 20፤9 እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ድንቅ ታምራት ያደርግ ነበርና።
ቅዱሳን እነርሱ ብቻ ሳይሆኑ ጥላቸውና ልብሳቸው ሳይቀር ይፈውሳል። የቅዱሳን ነገር ሲነሳ የማይዋጥላቸው ሰዎች ቢኖሩም እግዚአብሔር ሁለንተናቸውን ስላከበረው ቅዱሳን ነገራቸው ሁሉ ይፈውሳል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልብስ እንፈወሰ ሁሉ የቅዱስ ጳውሎስም ልብሱ ይፈውስ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል። ሐዋ 19፤11 እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር። የቅዱስ ጴጥሮስም ጥላው ፈዋሽ ነበር። ሐዋ 5፤15 ስለዚህም ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከእነርሱ አንዱን ይጋርድ ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋና በወሰካ ያኖሩአቸው ነበር።

 
2. ኢየሱስ ክርስቶስ አለምን ከራሱ ጋር አስታርቋል ቅዱሳን ደግሞ ያማልዳሉ
ምልጃ ማለት አንድን አካል ወክሎ በሌላ አካል ፊት ልመናን ማቅረብ ማለት ነው። በመንፈሳዊው አለም ምልጃ ለአንድ ሰው ወይም ሀገር ወደ እግዚአብሔር ልመናን ማቅረብ ነው። አንድ ሰው ስለሌላ ሰው ወደ እግዚአብሔር የሚያደርገው ልመናና ጸሎት ምልጃ ይባለል።

የተወደዳችሁ ምዕመናን ሆይ እንግዲህ እግዚአብሔር ያከበረውን ማን ይከሰዋል እግዚአብሔርስ እንዲፈውሱ ስልጣንን ከሰጣቸው ማን ሊቃወም ይችላል? ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሆን አናውቅምን?
ዛሬ አንዳንዶች ይህንን ፈውስ ለማስመሰል ጸጋው ሳይሰጣቸው የፈወሱ ለመምሰል ሲጣጣሩ እንመለከታለን። የሐሰት በሽተኞች አዘጋጂተው የሐሰት ክራንች አስይዘው በሐሰት ፈወስን የሚሉ የዘመኑ ሐሰተኛ ነቢያትን ማየት የተለመደ ሆኗል እኛ ግን እውነቱን ከሐሰቱ እንድንለይ እግዚአብሔር ማስጠንቀቂያ ስለሰጠን ከሐሰተኞች ማታለል እንጠበቅ። እግዚአብሔር ጸጋ የሰጣቸውን እውነተኞችን ቅዱስንም እናክብር።

ልመናን የሚቀበል ሐጢያትን የሚያስተሰርይ እግዚአብሔር ስለሆነ ምልጃ የሚቀርበው ወደ እግዚአብሔር ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይግባውና በስጋው ወራት በተመላለሰበት ጊዜ ለእኛ አርአያ ይሆነን ዘንድ ስለደቀ መዛሙርቱ እንዲሁም ስለጠላቶቹ ይጸልይ ነበር። የሐ 17፤1-26 ሉቃ 23፤34 ክርስቶስ ምንም እንኳን ራሱ እግዚአብሔር ቢሆንም እና ራሱ የመማርም ሆነ የመፍረድ ስልጣን ቢኖረውም ለእኛ አርአያ ይሆን ዘንድ ሲለምን እናየዋልን። ይህም እኛ እርስ በእርሳችን አንዱ ስለአንዱ እንዲለምንና እንዲማልድ ያስተምረን ዘንድ ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋው ወራት ቢጸልይም ቢለምንም እንኳን ከሞተና ከተነሳ በሗላ ልመናን ምልጃን የሚያደርጉ ቅዱሳን እንደሆኑ እንጂ ራሱ እንደማይለምን በአጭር ቃል አስቀምጧል።
ዮሐ 16፤26 በዚያን ቀን በስሜ ትለምናላችሁ፤ እኔም ስለ እናንተ አብን እንድለምን የምላችሁ አይደለሁም፤ በዚህም እነርሱ እንደሚለምኑ እንጂ እርሱ አብን በስጋው ወራት እንደነበረው ሁኔታ እንደማይለምን ተናግሯል። የኢየሱስ ክርስቶስን ትዕዛዝ ይዘውም ቅዱሳን ሲያማልዱ ኖረዋል አሁንም ያማልዳሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ ቅዱሳን እንደሚያማልዱ በግልጽ አስቀምጧል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቶስ አለምን ከራሱና ከአባቱ ጋር ካስታረቀ በሗላ በአሁኑ ጊዜ ቅዱሳን እንደሚያስታርቁ /እንደሚያማልዱ/ ሲናገር።
2ኛ ቆሮ 5፤18 ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ የማስታረቅ አገልግሎት የሰጠን ሲል ቅዱሳን አስታራቂዎች /አማላጆች/ መሆናቸውን ለመጥቀስ ነው። ቀጥሎም በእኛም የማስታረቅን ቃል አኖረ ብሎ ይናገራል። ቅዱሳን የማስታረቅን የማማለድን ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተቀብለዋልና። እንዲሁም ይህ ሐዋርያ ስለ ቅዱሳን ሲናገር ራሳቸውም ስለ እናንተ ሲያማልዱ፥ በእናንተ ላይ ከሚሆነው ከሚበልጠው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ይናፍቁአችኋል። 1ኛ ቆሮ 9፤14 ለምዕመናኑ የተመረጡ ቅዱሳን እንደሚማልዱ ሲያመለክት ነው።
2.1. የምልጃ መስራች ማን ነው?
አንዳንድ ሰዎች ምልጃን ሰዎች የፈጠሩት ይመስላቸዋል ነገር ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ምልጃን ለሰው ልጆች ያስተዋወቀ ራሱ እግዚአብሔር ነው። የአብርሃምን ሚስት ሳራን ከአብርሃም ለይቶ ለመገናኘት የፈለገውን ንጉሱን አቤሜሌክን እግዚአብሔር ከተቆጣው በሗላ እንድምርህ ይቅርታ እንዳደርግልህ አብርሃም ይጸልይልህ /ያማልድህ/ ብሎታል። ዘጽ 20፤7 አሁንም የሰውዬውን ሚስት መልስ፤ ነቢይ ነውና፥ ስለ አንተም ይጸልያል፥ ትድናለህም። እግዚአብሔር ራሱ አንተ ጸልይ እምርሃለሁ አላለውም እርሱ ይጸልይልህ አለው እንጂ። ሶስቱ የኢዮብ ወዳጆች ኢዮብን የሚያሰቀይም ነገር በተናገሩና እግዚአብሔርን ባሳዘኑ ጊዜ ራሱ እግዚአብሔር ወደ ኢዮብ ሂዱና ኢዮብ ስለእናንተ ያማልዳችሁ ሲላቸው እናያለን። ኢዮ 42፡8 ወደ ባሪያዬ ወደ ኢዮብ ዘንድ ሂዱ፥ የሚቃጠልንም መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ አሳርጉ፤ ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፥ እኔም እንደ ስንፍናችሁ እንዳላደርግባችሁ ፊቱን እቀበላለሁ።
እንግዲህ ከዚህ የምንመለከተው እግዚአብሔር ምንም እንኳን ማንንም የሚሰማ ቢሆንም እንኳን ምልጃ ደግሞ የእርሱ ፈቃድና ትዕዛዝ እንሆነና ቅዱሳን እንዲያማልዱ ፈቃድና ትዕዛዝ የሰጠ እርሱ መሆኑን አስረድቶናል።
ምልጃም ያስፈለገበት ዋናው ምክነያት እግዚአብሔር ከሐጢያተኞች ይልቅ የቅዱሳንን ስለሚሰማና የቅዱሳንን ልመና ለመፈጸም ደስ ስለሚለው ነው። 1ኛ ጰጥ 3፤12 የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፥ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው።
2.2. የቅዱሳን ምልጃ በአጠቃላይ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠ ቢሆንም የሚከተሉትን ጥቅሶች እንመልከት
እግዚአብሔር በአብርሃም ምልጃ አቤሜሌክን እንደፈወሰው ዘፍ 20፡ 17፤ አብርሃምም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም አቢሜሌክን ሚስቱንም ባሪያዎቹንም ፈወሳቸው፥ እነርሱም ወለዱ፤ አብርሃም ስለሰዶምና ገሞራ በእግዚአብሔር ፊት ማልዷል። ዘፍ 18፤20-33
ነቢዩ ኤልያስ አማልዶ የህጻኑን ነፍስ አስመልሷል።1ኛ ነገ 17፤17-24 እንዲሁም ኤልያስ አማልዶ ለሶስት አመት አልዘንብ ያለው ዝናብ እንዲዘንብ አድርጓል። 1ኛ ነገ 18፤30 ኤልሳዕ በምልጃው የሞተውን ልጂ አስነስቷል። 2ኛ ነገ 4፤18-36።
ኢዮብ እግዚአብሔር የልጆቹን ሐጢያት ይቅር ይል ዘንድ በእየእለቱ ሲማልድ እንመለከተዋለን /ኢዮ 1፤5/ ኢዮብ ለጓደኞቹ እንዲማልድ እግዚአብሔር እንዳዘዘና ኢዮብ እንደማለደም መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ኢዮ 42፡8።
ሙሴ የህዝብ መሪና ነቢይ ስለነበረ ጊዜውን በአጠቃላይ ያሳለፈው ለእስራኤል በመማለድ ነው። ሙሴ ለፈርኦን አማልዷል /ዘጸ 8፤8-15 ዘጸ 8፤25-31/
ሙሴ እስራኤል ጣኦት በማምለካቸው ምክነያት እግዚእብሔር ሊያጠፋቸው ስለተቆጣ ሙሴ እንዳይጠፉ አማልዶ አስምሯቸዋል/ዘጸ 32፤1-15/ ሙሴ እህቱና ማርያምና ወንድሙ አሮን ኢትዮጲያዊቷን በማግባቱ በተቆጡ ጊዜ እህቱን እግዚአብሔር በለምጽ ስለመታት አማልዶ አድኗታል /ዘሁ 12፤1-7/
ቀዳሚ ሰማዕት እስጢፋኖስ ስለገደሉት ሰዎች ተንበርክኮም። ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ እየጸለየ ብሎ ሲያማልድ እናየዋለን።/ሐዋ 7፤60/።
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምልጃ እንዲደረግም ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀመዝሙሩ ይነግረው ነበር።ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። 1ኛ ጢሞ 2፤1-2
የሰዎች ልጆች ልመናን ማቅረብ የሚችሉት በህይወት እያሉ ብቻ አይደለም ከዚህ ዓለም ካለፉም በሗላም በሰማይ ሆነው ልመናን ማቅረብ ይችላሉ። ለምሳሌ ጌታችን በሉቃ 16፤20-31 እንዳስተማረው ሐጢያተኛው ነዊየ በምድር ስላሉ ስለሐጢያተኞች ወንድሞቹና ወገኖቹ ሲማልድ እናየዋለን። ከዚህ የምንረዳው እንኳን ቅዱሳን ሐጢያተኞች ከሞቱ በሗላም ሳይቀር ለወገኖቻቸው ምልጃን እንደሚያቀርቡ ነው። ሆኖም እግዚአብሔር የሐጢያተኞችን ምልጃ አይቀበልም በህይወታቸው እርሱን አላገለገሉምና። እንዲሁም በራዕ 6፤10 ላይ ቅዱሳኑ ወደ እግዚአብሔር ልመናን ሲያቀርቡ እንመለከታለን። እግዚአብሔር የህያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ ስላልሆነ ቅዱሳን በስጋ ቢሞቱ እንኳን ከዚህ አለም ተሰናበቱ እንጂ በእግዚአብሔር ዘንድ ህያዋን ናቸው። ለዚህ ነው ጌታችን ሲያስተምር በማቴ 22፤31-32እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም። አብርሃም፤ ይስሃቅና ያዕቆብ በስጋ ከሞቱ በሗላ ሳይቀር ጌታ ህያዋን ይላቸዋል። እነርሱ ከእግዚአብሔር ጋር ህይወታቸውን ያሳለፉ በመሆናቸው ህያዋን ይባለሉና። አማላጂነታቸው ከእኛ ጋር ትሁን። አሜን።

3. ኢየሱሰ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ ነው ቅዱሳንም የጸጋ አማልክት ይባላሉ
ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይግባውና ምንም እንኳን ሰዎች በሚገባ ባይረዱትም እርሱ አምላክ ነው። እንዲያውም አይሁድ ሞት እንደፈረድበት ካስቀመጧቸው ክሶች ውስጥ ዋናው አንተ ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ታደርጋለህ የሚል ነበር።ዮሐ 10፤33 አይሁድም። ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት። ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ስለመሰላቸው አምላክነቱን በሚገባ ለመረዳት አልቻሉም። እርሱ በደከመው ስጋ የባርያን ምሳሌ ይዞ መጥቷልና። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ ፊሊ 8፤6-7 እርሱ ራሱን ዝቅ አድርጎ በመምጣቱ ሰዎች አምላክነቱን መረዳት ባይችሉም እርሱን አምላክ ከመሆን አላገደውም። ዛሬም እርሱ በደካማ ስጋ ተገልጦ ያደረጋቸውን ነገሮች ይዘው ሰዎች ኢየሱስ ፍጡር ነው ቢሉ ፍጡር ሊሆን አይችልም እርሱ ፈጣሪ ነውና። እርሱ አማላጂ ነው ቢሉት ሊሆን አይችልም እርሱ ፈራጂ ነውና። የሚያጸድቅም መኮነንም የሚችል እርሱ ነውና።2ኛ ጢሞ 4፡ 1 ምንም እንኳን የማያምኑ ሰዎች አምላክ አይደለም ቢሉት መጽሐፍ ቅዱስ ግን የክርስቶስን አምላክነት ይገልጣል። ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ 9፤ 5 እርሱ ከሁሉ በላይ ሆኖ የተባረከ አምላክ ነው።ሲል ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ በ1ኛ ዮሐ 5፤ 21 እርሱ እውነተኛና የተባረከ አምላክ ነው እንዲሁም ቶማስ በዮሐ 20፤ 8 ቶማስም ጌታየ አምላኬ ብሎ መለሰለት እንዲሁም ቅዱስ ጴጥሮስ 2ኛ ጴጥ 1፤ 1 በአምላካችንና በመድሓኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማለት የጌታችንን አምላክነት ገልጠዋል።ነቢዩ ዳዊት ገና ክርስቶስ ሳይወለድ እርሱን አምላክ እንዳለው ሐዋርያው ሲጠቅስ በዕብ 1፤ 11 ስለ ልጁም አምላክ ሆይ ዙፋንህ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም የጸና ነው።
እንግዲህ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ ሁሉ ቅዱሳንን ደግሞ እርሱ ራሱ የጸጋ አማልክት ብሎ ሾሟቸዋል። እግዚአብሔር ራሱነው ቅዱሳንን አማልክት ያላቸው። በመዝ 82፤1 እግዚአብሔር በአማልክት ማኅበር ቆመ፥ በአማልክትም መካከል ይፈርዳል። በአማልክት መካከል ሲል ሌሎች አምላኮች አሉ ማለት ሳይሆን ቅዱሳንን ነው አማልክት ያላቸው። እንዲሁም ቁጥር 6 ላይ 6 እኔ ግን። አማልክት ናችሁ፥ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ፤ በዚህም መሰረት አማልክት የሚለው ቅዱሳንን ነው። ይህንን ኢየሱስ ክርስቶስ ጠቅሶ ተናገግሯል በዮሐ 10፤34-35 ኢየሱስም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው። እኔ። አማልክት ናችሁ አልሁ ተብሎ በሕጋችሁ የተጻፈ አይደለምን?መጽሐፉ ሊሻር አይቻልምና እነዚያን የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን አማልክት ካላቸው፥ በዚህም የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸው ከእግዚአብሔር ጋር የተነጋገሩ ቅዱሳን አማልክት እንደተባሉ ያስረዳል።
እግዚአብሔር ነቢዩ ሙሴን በፈርኦን ላይ አምላክ አድርጎ እንደ ሾመው ሲናገር ዘጸ 7፤1 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። እይ፥ እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል። በዚህም በፈርኦን ላይ ስልጣን ኑሮት ያንን ሁሉ ታምር አድርጓል።
ወገኖቼ ሆይ ለቅዱሳን እግዚአብሔር የሰጣቸው ክብር ምነኛ ድንቅ ነው። ዛሬ ሰዎች የቅዱሳን ክብር ሊያቃልሉ ቢፈልጉም አግዚአብሔር ግን በሚሰጠው ጸጋ የማይቆጭ ነው። እርሱን ላገለገሉት እንደልቡም ለተገዙለት ቅዱሳን እግዚአብሔር ምን ያክል ክብር እንዲሚሰጥ እናያለን ቅዱሳንን አማልክ አድርጎ ሲሾም ተመልክተናልና።
4. ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን አዋቂ ነው ቅዱሳንም እግዚአብሔር በሰጣቸው ጸጋ የተሰወረን ነገር ያውቃሉ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በባህርይው ሁሉን ያውቃል። አምላክ ስለሆነ የሚሰወረው አንዳች የለም በእርሱ ዘንድ የራሳችን ጸጉር እንኳን ሳይቀር ይታወቃል። ጌታ ልብንና ኩላሊትን ይመረምራል አዕምሮ ያመላለሰውን ያውቃል።ራዕ 2፤23 አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ኵላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ። እንዲሁም በዮሐ 2፤24-25 ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፤ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና። ይላል። በዚህም ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን አዋቂ እንደሆነ እንረዳለን።
ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን ይመስሉ ዘንድ ለቅዱሳን ክብርን ሰጥቷቸዋልና። ለዚህም ቅዱሳን በሰው ልብ ያለውን ሳይቀር በመንፈስ ቅዱሰ ተረድተው ያውቁ እንደነበር እንረዳለን። ቅዱስ ጴጥሮስ ሐናኒያና ሰጲራ እቤታቸው ሆነው የተነጋገሩትን ሚስጢር ማንም ሳይነግረው አውቆታል። ሐዋ 5፤1-11 እንዲሁም ቅዱሱ የእግዚአብሔር ሰው ኤልሳ የሶሪያ ንጉስ የሚሰራውን ስራ እስራኤል ውስጥ በአንዲት ጎጆ ውስጥ ሆኖ ማወቅ ይችል ነበር።2ኛ ነገ 6፤12 ከባሪያዎቹም አንዱ። ጌታዬ ሆይ፥ እንዲህ እኮ አይደለም፤ ነገር ግን በእልፍኝህ ውስጥ ሆነህ የምትናገረውን በእስራኤል ዘንድ ያለ ነቢይ ኤልሳዕ ለእስራኤል ንጉሥ ይነግረዋል አለ። እግዚአብሔር መንፈሱን ስለሰጣቸው ቅዱሳን በሰው ልብ የማይታሰበውን ያውቃሉ። ቅዱሳን እውቀታቸው ከመንፈስ ቅዱስ ነው። ለዚህም ነው አባቶቻችን የእመቤታችን ልቦና እንደ አምላክ ልብ ነው ብለው የሚናገሩት እርሷ ጸጋን የተመላች ስለሆነች እውቀትን የሚገልጥላት በመንፈስ ቅዱስ ነውና። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም እኛ ግን የክርስቶስ ልብ አለን። 1ኛ ቆሮ 2፤16 ይላል እግዚአብሔር እውቀትን ገልጦላቸዋልና። ሰዎች በተፈጥሯቸው ማወቅ የማይችሉትን ቅዱሳን እግዚአብሄር በሰጣቸው ስልጣን መሰረት ሲያውቁ እንመለከታለን።
5. ኢየሱስ ክርስቶሰ ፈራጂ ነው ቅዱሳንም እርሱ በሰጣቸው ስልጣን ይፈርዳሉ
ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉስ አምላክ ጌታ ስለሆነ ፈራጂ ነው። በሐጥአን የሚፈርድባቸው ለጻድቃን የሚፈርድላቸው ፍርድን የሚሰጥ እርሱ ኢየሱስ ነው። 2ኛ ጢሞ 4፡ 1 በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤ በህያዋንና በሙታን ላይ የሚፈርደው እርሱ ክርስቶስ ነው። ፍርድን የሚሰጥ እርሱ እግዚአብሔር የሆነ ክርስቶስ ነው። ከእርሱ ፍርድ ይወጣል እንጂ ልመና አይወጣም።

2ኛጢሞ 4፤ 8 ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ ጻድቅና ፈራጂ ነው። ፍርዱም በአንድና በሁለት ሰው የሚወሰን አይደለም በሁሉም ላይ የሚፈርደው እርሱ ነው። ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ያለው። መገለጡን ለሚወዱ ሁሉ ይፈርድላቸዋልና።

2ኛ ቆሮ 5፡ 10 መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፥ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና። መፅሐፍ ቅዱስ ፍርድ እንዳለ ይነግረናል። ይህን ፍርድ ደግሞ በእያንዳንዳችን ላይ የሚደረግ ነው። በእያንዳንዳችን የሚፈረደውን ፍርድ የሚፈርደው እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ታዲያ ኢየሱስ ሲፈርድ መጀመሪያ ለምኖ ይሆን የሚፈርደው ? አይደለም ኢየሱስ የሚፈርደው በስራችን መጠን ነው። እርሱ እኛነታችንን ያውቃል በስራችን መጠንም ይፈርዳል።

ራዕ 22፤ 12፡ እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ :: ክርስቶስ ስራችንን ስለሚያውቅ እንደስራችን መጠን እንደ ሃይማኖታችን መጠን ፍርድን ይሰጣል። ፍርድን ሲሰጥ ሰዎች አማልደን ይሉት ይሆንን ? አይባልም እርሱ ፈራጅ እንጂ አማላጂ አይደለምና። እንዲያውም ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው ፍርድን የሚያደርገው እርሱ ኢየሱስ እንጂ አብ አይደለም። ይህ ሲባል የአብና የወልድ ፈቃድ የተበለያየ ነው ማለት አይደለም የአብም ሆነ የወልድ ፈቃድ አንድ ነው ሆኖም ፍርዱን የሚሰጠው የሚፈርደው እርሱ ኢየሱስ ነው። አብ በማንም አይፈርድም ፍርድ የእርሱ የወልድ ስልጣን ነው። ዮሐ 5-22-23 ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም :: ፈራጂ ወልድ ከሆነ እንግዲህ ወልድ የሌለው ስልጣን አለ ልንል እንችላለን ? የለም ወልድ ራሱ ነው የሚፈርደው የሚጸድቁትንም ሆነ ወደ ኮነኔ የሚሄዱትን የሚለይ የሚፈርድ እንደ ስራቸው የሚያስረክብ እርሱ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ጌታችን በሰማይና በምድር ፈራጂ እንደሆነ ሁሉ ቅዱሳንንም ይፈርዱ ዘንድ ስለጣንን ሰጥቷቸዋል። ቅዱሳንን ይፈርዱ ዘንድ ስልጣንን የሰጣቸው እራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማቴ 19፤28 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ። ቅዱሳን ማማለድ አይደለም እንዲፈርዱ እርሱ እግዚአብሔር ሾሟቸዋል ታዲያ እግዚአብሔርን ተሳስተሃል ብሎ ማን ይቃወመዋል እርሱ የወደደውን መስራት ይችላልና። እርሱ ካከበራቸውስ ማን ሊቃወማቸው ይችላል።
የተወደዳችሁ አንባቢያን ሆይ ቅዱሳን ኢየሱስ ክርስቶስን የመሰሉት እንዲሁ አይደለም። እነርሱ በህይወታቸው እግዚአብሔርን ስላስቀደሙ ከዚህ ዓለም ተድላና ደስታ ይልቅ እርሱን ስለወደዱ ቃሉን እለት እለት እያስታወሱ በህጉ ስለተጓዙ ነው። እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስን በመልካም ስራው በመከተል እርሱ እንደ ጾመ ስለጾሙ እርሱ እንደጸለየ ስለጸለዩ እርሱ የሚጠሉትን እንደወደደ ጠላቶቻቸውን ስለወደዱ እርሱ ድሆችንና ችግረኞችን እንዳከበረ የሰውን ልጂ ሁሉ ስላከበሩ እርሱ ደግሞ ክብራቸውን አበዛ በጸጋ ላይ ጸጋ ሰጣቸው። እንደዚያ ባይሆን ኖሮማ ቅዱሳን እንደእኛ ሰዎች ነበሩ ነገር ግን እንደእኛ ሰው ሲሆኑ በእምነታቸው ምክነያት ሰው የማይሰራውን ስራ ሰሩ። እኛም ሐዋርያው እንደተናገረ ቅዱሳንን ለመምሰል እንትጋ። ፍቅርንና ትህትናን እንላበስ ወንድሞቻችንን እንወደድ የተቸገሩትን እንርዳ የእግዚአብሔርን ቃል እንማር ቃሉንም ለማያውቁና ለማያምኑ እናስተምር ያን ጊዜ ቅዱሳንን እንመስላለን።ያን ጊዜ እግዚአብሔር ይባርከናል ያከብረናልም።
ቃሉን አውቀን በህይወታችን ተርጉመን እንድንጠቀም የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጂነት አይለየን!!!

2 Responses to “ቅዱሳን እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ”

  1. nebiyou Samuel Says:

    how st. Mary became intercessor? you don’t need any mediator in b/n you and your God,you have the right to communicate with God: It is not by yourself, it is because of His work.16በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና። 17ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።

  2. Anonymous Says:

    That is your view. But God’s word shows us that there are mediators. Abraham mediated the people of sedom, Job intercessors his children and it was the will of God for the saints to intercede on behalf of us.

    However it doesn’t mean you cannot pray directly to God. That is right. You have the right to pray to God. However the teaching of intercession is biblical and correct. Any one who doesn’t accept this teaching is having heretic.

Leave a comment